በመተከል ዞን ዘላቂ ሰላም የመፍጠር ስራ በትኩረት እየተከናወነ መሆኑን ኮማንድ ፖስቱ ገለጸ - ኢዜአ አማርኛ
በመተከል ዞን ዘላቂ ሰላም የመፍጠር ስራ በትኩረት እየተከናወነ መሆኑን ኮማንድ ፖስቱ ገለጸ
አዲስ አበባ ሰኔ 25/2013 (ኢዜአ) በመተከል ዞን ተፈናቃዮችን ወደ መኖሪያ ቀያቸው የመመለስና በአካባቢው ዘላቂ ሰላም የመፍጠር ስራ በትኩረት እየተከናወነ መሆኑን የዞኑ የተቀናጀ ግብረ ኃይል ኮማንድ ፖስት ሰብሳቢ ሌተናል ጀኔራል አስራት ዴኔሮ ገለጹ።
ግብረ ኃይሉ በማንቡክ ከተማ በጊዜያዊ መጠለያ የሚገኙ ዜጎች ያሉበትን ሁኔታ በስፍራው ተገኝቶ ተመልክቷል።
የኮማንድ ፖስቱ ሰብሳቢ ሌተናል ጀኔራል አስራት ዴኔሮ፤ በዞኑ የተፈናቀሉትን መልሶ የማቋቋም፣ እርቀ ሰላም በማከናወን ዘላቂ ሰላምና አብሮነትን የማጠናከር ስራ እየተከናወነ መሆኑን ገልጸዋል።
በየደረጃው ያለ አመራር ከሚያደርገው የደህንነት ጥበቃ፣ የክትትልና ድጋፍ ስራ በተጨማሪ ህብረተሰቡን ወደ ቀደመ አብሮነቱ ለመመለስ እየተሰሩ የሚገኙ የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት ስራዎች ውጤት ማምጣታቸውን ጠቅሰዋል።
የጸጥታ ሃይሉ የዜጎችን ደህንነት ለመጠበቅ እያደረገ ስላለው ተግባር ሌተናል ጀኔራል አስራት አድናቆታቸውን ገልጸዋል።
በአንዳንድ ሰብዓዊ የእርዳታ እደላ ሂደት ላይ ያለውን መጓተት እንደሚገነዘቡ ገልጸዋል።
በቦታ እርቀትና በማጓጓዝ ሂደት የሚስተዋሉ ጉድለቶችን በማረም ድጋፉ ከአመራርና ከተመላሽ ዜጎች ጋር በመመካከር በወቅቱ እንዲሰራጭ እንደሚደረግ አረጋግጠዋል።
የአገር ሽማግሌና የኃይማኖት አባቶች መንግስት ከሚሰራው የእርቀ ሰላም ኮንፈረንስ በተጨማሪ ቂምና ቁርሾን ለማስቀረት የይቅር እንባባል ስራን በቀጣይነት ማከናወን ይኖርባቸዋል ብለዋል።
ህብረተሰቡም ከጸጥታ ኃይሉ ጋር በዘላቂነት በቅንጅት መስራት እንዳለበት ሌተናል ጀኔራሉ ገልጸዋል።
ግብረ ሃይሉን ጨምሮ የዞንና የወረዳ አመራርና የስራ ኃላፊዎች ከመተከል ዞን ዳንጉር ወረዳ የተለያዩ ቀበሌዎች ተፈናቅለው በማንቡክ ከተማ ጊዜያዊ መጠለያ ማዕከል የሚገኙ ዜጎችን ጎብኝቷል።
የመተከል ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ጋሹ ዱጋዝ፤ በማዕከሉ ለሚገኙ ዜጎች የሚደረገው ሰብዓዊ ድጋፉ በተቀላጠፈ መልኩ እንዲደርሳቸው እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
በከባድ ነፋስ ሳቢያ የፈረሱ የተወሰኑ ጊዜያዊ የመጠለያ ድንኳኖች በፍጥነት እንደሚስተካከሉም አረጋግጠዋል።