ቀጥታ፡

የፌዴራል መንግስት ለትግራይ ህዝብ የሰጠውን የጥሞና ጊዜ እንደሚደግፉ የአሶሳ ነዋሪዎች ገለጹ

አሶሳ ፤ ሰኔ 25 / 2013 (ኢዜአ) የትግራይ ህዝብ ሰላሙን በራሱ እንዲወስን በፌደራል መንግስት የተሰጠውን የጥሞና ጊዜ እንደሚደግፉ በቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልል አሶሳ ከተማ አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ ነዋሪዎች ገለጸ።

ከነዋሪቹ መካከል አቶ ሞላ ጌታነህ  እንዳሉት፤ ህወሓት በሃገር መከላከያ የሰሜን እዝ ላይ ካደረሰው ጭካኔ የተሞላበት ጥቃት ጀምሮ ጉዳዩን በአንክሮ ሲከታተሉት ቆይተዋል።

በአሸባሪነት የተፈረጀው የህወሓት ቡድን በክልሉና ህዝቡ ላይ ጉዳት ማድረሱንና መንግስትም ክልሉን መልሶ ለማልማት ሲሰራ እንደነበር የጠቀሱት አቶ ሞላ፣ ይህም ሆኖ በትግራይ ሰላምን በሚፈለገው መጠን ማምጣት እንዳልተቻለ ተናግረዋል፡፡

"ህብረተሰቡ ይህ የጥፋት ቡድን ለ30 ዓመታት በሀገር ላይ ያደረሰውን ጥፋት ሊገነዘበው ይገባል" ብለዋል፡፡

ህብረተሰቡ ሠላሙን በራሱ እንዲወስን እና የክረምት እርሻውን ተረጋግቶ እንዲያከናውን በማሰብ ሠራዊቱ ከመቀሌ ከተማ እንዲወጣ መደረጉ ተገቢ እና አስፈላ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

"ከዚህ በኋላ ብጥብጥ እና ሁከት ሊበቃ ይገባል" ያሉት ነዋሪው፣ የፌዴራል መንግስት የትግራይ ህዝብ በአግባቡ እንዲጠቀምበት የሰጠውን የጥሞና ጊዜ እንደሚደግፉ ገልጸዋል።

"ፓርቲ ይቀያየራል፤ ህዝብ ይቀጥላል" የሚሉት አቶ ሞላ፣ መልካም የሚሠራ ፓርቲንም ሆነ መንግስት በመደገፍ ማበረታታት ተገቢ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡

እንደ ነዋሪው ገለጻ፤ የኢትዮጵያ ወደፊት መራመድ ያላስደሰታቸው አካላት የህዝብን ሰላም ለመንሳትና ሀገር ለማፍረስ እየሰሩ ይገኛሉ።

"ይህን ፍላጎታቸውን ለማሳካት ደግሞ የውስጥ ባንዳዎችን ተጠቅመው እርስ በርስ ለማባላት ተግተው እየሰሩ ነው" ሲሉም አክለዋል፡፡

"ኢትዮጵያ አሁን ትኩረት ልትሰጣቸው የሚገቡ ሌሎች አጃንዳዎች አሉ" ያሉት ደግሞ ሌላው የከተማዋ ነዋሪ አቶ ሰይድ መሃመድ ናቸው፡፡

ሌሎች ቀዳሚ አጀንዳዎች በመኖራቸው ምክንያት መንግስት የሃገር መከላከያ ሠራዊት ከመቀሌ እንዲወጣ ማድረጉን እንደሚደግፉ  ገልጸዋል፡፡

ይህንንም መላው የኢትዮጵያ ህዝብ በሚገባ ይረዳዋል የሚል እምነት እንዳላቸውም ተናግረዋል።

"ሠራዊቱ ከመቀሌ እንዲወጣ መደረጉን የማይቀበል አካል ካለ አይገርምም" ያሉት አቶ ሰይድ፣ የሕዳሴው ግድብን ጨምሮ ሌሎች ፕሮጀክቶች እንዳይሳኩ የሚጥሩ አካላት እንዳሉም አስታውሰዋል።

የኢትዮጵያን ህዝብ እና መንግስት ትኩረት በራሳቸው አቅጣጫ ለመምራት ሌት ተቀን እየሰሩ መሆናቸውንም አመልክተዋል።

ሼህ እንድሪስ አህመድ በበኩላቸው፤  "አሸባሪው ህወሓት ኢትዮጵያዊያንን በዘር፣ ጎሳ እና መንደር ለመከፋፈል ለዓመታት ሲሠራ ነበር" ብለዋል፡፡  

መንግስት ክልሉን መልሶ ለማልማት ካወጣው ከፍተኛ ገንዘብ በተጨማሪ የህይወት መስዋዕትነት መከፈሉን ገልጸው፣ ከዚህ አንጻር የሚፈለገውን ሠላምና መረጋጋት በክልሉ ማምጣት እንዳልተቻለ ተናግረዋል።

ሀገሪቱ ካለችበት ነባራዊ ሁኔታ ጋር በማየት ሁኔታዎችን ማስተካከል፣ የኢኮኖሚውን ጫና መቀነስና  የሠራዊቱን ህይወት በተሻለ መታደግ የሚቻልበትን አማራጭ መውሰድ ተገቢ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ለትግራይ ህዝብም ጉዳዩን ቆም ብሎ እንዲያስብ የጥሞና ጊዜ መሰጠቱ የሚደገፍና ሊጠቀምበት እንደሚገባም ሼህ እንድሪስ ተናግረዋል።

ወይዘሮ ነበሩ ጨርቆሴ በሰጡት አስተያየት፤ መንግስት የትግራይ ህዝብ የእኔ ወገን ነው በሚል ባለፉት ወራት ክልሉን መልሶ ለመገንባት ሲሰራ መቆየቱን አስታውሰዋል።

ሰሞኑን በተሰጠው መግለጫ የፌዴራል መንግስት ለክልሉ ከፍተኛ መዋዕለንዋይ ማፍሱስን እንደተረዱና ይህም ለህዝቡ ያለውን አሳቢነት እንደሚያሳይ ገልጸዋል

አሸባሪው ጁንታ በተደጋጋሚ የሠላም ሽምግልና ቀርቦላቸው እንደነበር ያስታወሱት ወይዘሮ ነበሩ፣ "በወቅቱ ጥሪውን ተቀብሎ ቢሆን ኑሮ በሰውና ሀገር ሃብት ላይ የደረሰውን ጉዳት መታደግ ይቻል ነበር" ብለዋል፡፡

መንግስት የመከላከያ ሠራዊት ከመቀሌ ከተማ እንዲወጣ ማድረጉን እንደሚደግፉት ገልጸው፣ ይህም በተለይ የክልሉ ህዝብ ጉዳዩን በተሻለ ማጤን እንደሚያስችለው ተናግረዋል፡፡

ሌላው የከተማዋ ነዋሪ ምክትል ኮማንደር ዶሴና ዶራ እንዳሉት፤ ሠራዊቱ መውጣቱ ኢትዮጵያ ሌላ የውጪ ጥቃት እንዳይፈጸምባት ለመመከት ትኩረቱን እንዲሰበስብ ያደርገዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም