የለውጥ ሂደት እንዳይደናቀፍ ህዝብን ያሳተፈ የሠላምና ፀጥታ ስራ መጠናከር እንዳለበት ተመለከተ - ኢዜአ አማርኛ
የለውጥ ሂደት እንዳይደናቀፍ ህዝብን ያሳተፈ የሠላምና ፀጥታ ስራ መጠናከር እንዳለበት ተመለከተ
ሀዋሳ ሰኔ 24/2013 (ኢዜአ) በሀገሪቱ የተጀመረው የለውጥ ሂደት እንዳይደናቀፍ ህዝብን ያሳተፈ የሠላምና ፀጥታ ስራ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ተመለከተ።
ምርጫው በስኬት መጠናቀቁን ተከትሎ የኦሮሚያ፣ሲዳማና ደቡብ ክልሎች የፀጥታ አካላት የጋራ የምክከር፣ የእውቅናና ምስጋና መድረክ ዛሬ በሀዋሳ ከተማ ተካሂዷል።
የሲዳማ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ደስታ ዴዳሞ በመድረኩ እንደገለጹት፤ ስድስተኛው ጠቅላላ ምርጫ በስኬት እንዲጠናቀቅ የፀጥታ መዋቅሩ የሚያኮራ ስራ አከናውኗል።
በተለይ ለምርጫው ስኬታማነት በየደረጃው ያለው የፀጥታ ኃይል ተልዕኮውን በተገቢው መንገድ ተወጥቷል፤ ይህም ኢትዮጵያ እንድታሸንፍ አስችሏል ብለዋል።
ከድህነት ለመውጣትና ለኑሮ የምትመች ሃገር ለመገንባት የሰላም አስፈላጊነት ቀዳሚ መሆኑን የተናገሩት ርዕሰ መስተዳድሩ ፤ በተለይ በሀገሪቱ የተጀመረው የለውጥ ሂደት እንዳይደናቀፍ ህዝብን ያሳተፈ የሰላምና ጸጥታ ስራ አጠናክሮ መስቀጠል እንደሚገባ አመልክተዋል።
ጸጥታ መዋቅሩ በተገቢው ተደራጅቶ በመንቀሳቀሱ ክልሉን የሰላም ቀጠና ማድረግ መቻሉንም ርዕሰ መስተዳድሩ ገልጸዋል።
የሲዳማ ክልል ሰላምና ጸጥታ ቢሮ ኃላፊ አቶ አለማየሁ ጢሞቲዎስ በበኩላቸው፤ ምርጫው በሠላም እንዲጠናቀቅ የፀጥታ ኃይሉ ሌት ተቀን ተግቷል ብለዋል።
የጸጥታ ሃይሉ የተልዕኮ እንጂ የዓላማ ልዩነት የለውም ያሉት አቶ አለማየሁ፤ ከአጎራባች ክልሎችና መከላከያ ሰራዊት እስከ ታችኛው የጸጥታ መዋቅር የተከናወነው ቅንጅታዊ ስራ በፖለቲካ ፓርቲዎች ጭምር እውቅና የተሰጠው መሆኑን ተናግረዋል።
መድረኩ የተዘጋጀውም በምርጫ ወቅት ያጋጠሙ ጠንካራና ደካማ ጎኖችን በመገምገም በቀጣይ የተሻለ ስራ ለመስራት የሚያስችል አቅጣጫ ለማስቀመጥ መሆኑን ገልጸዋል።
የኦሮሚያ ክልል ሰላምና ጸጥታ ቢሮ ኃላፊ አቶ ጅብሪል መሐመድ ባለፉት ስድስት ወራት በሠላም ዙሪያ በጋራ በተደረገው ጥረት በአጎራባች አካባቢዎች አስተማማኝ ሰላምና አንድነት በማስፈን ህዝቡ ለልማቱ በጋራ ማትጋት መቻሉን ተናግረዋል።
ከሲዳማና ደቡብ ክልሎች አጎራባች ዞኖች ጋር የተከናወነው ስራ በምርጫው ውጤታማነት ተረጋግጧል፤ በሂደቱ በርካታ ትምህርቶች ቀስመናል ብለዋል።
የእውቅናና ምስጋና መድረክ መዘጋጀቱ በቀጣይ ለምንሰራው ስራ አቅም ይሆነናል ያሉት ደግሞ በመከላከያ ሠራዊት የደቡብ ዕዝ ጠቅላይ መምሪያ የመረጃ መምሪያ ተወካይ ኮሌኔል አድማሱ ደፋር ናቸው።
ምርጫው ሰላማዊና ዴሞክራሲዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ የሲዳማ ክልል በሚያወጣቸው ፕሮግራሞች በመሳተፍ የ በቅንጅት መስራታቸውን ተናግረዋል።
በመድረኩ ለምርጫው ስኬታማነት የተሻለ አፈጸጸም ላበረከቱ ተቋማትና ግለሰቦች እውቅናና ሽልማት ተበርክቶላቸዋል።