"እርካብና መንበር" በተሰኘው መጽሐፍ ላይ ውይይት ተካሄደ

133
አዲስ አበባ ሐምሌ 29/11/2010 "እርካብና መንበር" በተሰኘው መጽሐፍ ላይ ዛሬ በአዲስ አበባ ውይይት ተካሄደ። ብሄራዊ ቤተ ማዛግብትና ቤተ መጻሕፈት ኤጀንሲ፣ ጀርመን የባህል ማእከልና እናት ማስታወቂያ በትብብር በሚያዘጋጁት ወርሃዊ መድረክ ላይ ቀርቦ ውይይት የተደረገበት 'እርካብና መንበር' መጽሃፍ 'ዲርኣዝ' በሚል የብዕር ስም የተጻፈ መጽሐፍ ነው። በብሄራዊ ቤተ ማዛግብትና ቤተ መጻሕፈት ኤጀንሲ ለውይይት ሲቀርብ የውይይት መነሻ ሃሳብ የቀረበው በታሪክ ምሁሩ አቶ ብርሃኑ ደቦጭ ነው። እንደ አቶ ብርሃኑ ማብራሪያ፤ የመጽሃፉ አጠቃላይ ይዘት ከአጼ ቴዎድሮስ አንስቶ የነበረውን ስረዓተ መንግስታት የሚያነሳና ስለ ርዕዮተ ዓለም አስተያየት የሚሰጥ ነው። 'ርዕዮት ዓለም ሃይማኖት አይደለም የሚል እምነት ይንጸባረቅበታል' ያሉት አቶ ብርሃኑ በይበልጥ ስለ ፍቅርና መልካም ማንነት ያብራራል። በተለይ ስልጣንን ልምምድ ለሚያደርጉ መሪዎች መልእክት ያለው መጽሃፉ፤ ሞት የማይቀር መሆኑን በማሰብ ማንም ሰው በዘመኑ ሲኖር የተሰጠውን ኃላፊነት በተሰጠው ጊዜ በትክክልና በኃላፊነት መስራት እንዳለበት እንደሚገልጽ የታሪክ ባለሙያው ተናግረዋል። ከመድረክ በተነሳው የመጽሃፉ ሃሳብ ላይም በስፍራው የተገኙት የጥበብ ቤተሰቦችና የኪነ ጥበብ ባለሙያዎች ተወያይተውበታል። በውይይቱም በመጽሃፉ ይዘት ውስጥ ያሉትን ረቂቅ ሃሳብ በማንሳትና እያንዳንዱን ምዕራፍ በመጥቀስና በማብራራት ተወያይተዋል። በዕለቱ ተሳታፊ ከነበሩት ከያኒት አስቴር በዳኔ በሰጠችው አስተያየት የመጽሃፉ ደራሲ መልካም ስብዕና ያላቸው እንደሆኑ ተናግራለች። እርካብና መንበር በተሰኘው መጽሃፍ ላይ በተደረገው ውይይትና በርካታ ከመጽሃፉ ጭብጥ ጋር የተያያዙ ሃሳቦች ተነስተዋል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም