በኦሮሚያ ክልል ከ5 ነጥብ 1 ቢሊየን ብር በላይ በሆነ ወጪ የተገነቡ ፕሮጀክቶች ለአገልግሎት በቅተዋል

82

አዲስ አበባ፤ ሰኔ 24 ቀን 2013 (ኢዜአ) በኦሮሚያ ክልል እየተጠናቀቀ ባለው በጀት ዓመት ከ5 ነጥብ 1 ቢሊየን ብር በላይ በሆነ ወጪ የተገነቡ የተለያዩ ፕሮጀክቶች ለአገልግሎት መብቃታቸውን የኦሮሚያ ከተማ ልማትና ቤቶች ቢሮ አስታወቀ።

የኦሮሚያ ከተማ ልማትና ቤቶች ቢሮ ኃላፊ አቶ ጀማል ከድር፤ በበጀት ዓመቱ ከ5 ነጥብ 1 ቢሊየን ብር በላይ ወጪ ተደርጎባቸው የተገነቡ የተለያዩ ፕሮጀክቶች ለአገልግሎት መብቃታቸውን ገልጸዋል።

የተገነቡት ፕሮጀክቶች 3 ሺህ 674 ሲሆኑ 1 ሺህ 409ኙ ከ3 ነጥብ 8 ቢሊየን ብር በላይ በመንግሥትና አጋር ድርጅቶች ወጭ የተሰሩ መሆናቸውን ገልጸዋል።

2 ሺህ 764 ፕሮጀክቶች ደግሞ ከ1 ቢሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጭ በህብረተሰቡ ተሳትፎ የተሰሩ መሆናቸውን አቶ ጀማል ገልጸዋል።

ከዚህም በተጨማሪ በበጎፈቃድ አገልግሎት 1 ነጥብ 3 ቢሊየን ብር በሆነ ወጪ የተለያዩ ተግባራት በተለይ በከተሞች ተሰርተዋል ነው ያሉት።

በ61 ከተሞች የውስጥ ለውስጥ መንገድ፣ ትምህርት ቤቶች፣ በሁሉም ከተሞች የመዝናኛ ሥፍራዎች፣ የመንገድ ዳር መብራት፣ የንጹህ መጠጥ አቅርቦት፣ የወጣት ማዕከላት፣ ቤተ- መጽሐፍት፣ እና ሌሎች ሥራዎች መሠራታቸውን ጠቁመዋል።

ከዚህ በተጨማሪም 12 የከተማ ፓርኮች በ67 ሄክታር መሬት ላይ በ160 ሚሊየን ብር ተሰርተው ለአገልግሎት መብቃታቸውን ተናግረዋል።

በአዳማ፣ዱከም፣ ገላን፣ ባቱ፣ ጅማ፣ ሻሸመኔ እና ሌሎች ከተሞች ላይ በህብረተሠቡና በባለሀብቱ ተሳትፎ የከተማ ፓርኮች ተገንብተዋል።

በወንዞች ዳርቻ ልማትም በጅማ ከተማ በአዌቱ ወንዝ ላይ በሦስት ዓመታት የሚጠናቀቅ የ600 ሚሊየን ብር ፕሮጀክት የመጀመሪያ ምዕራፍ ተጠናቆ ለአገልግሎት ክፍት መሆኑ ተጠቁሟል።

ከተሞች ለኑሮ ምቹ፣ ጽዱና ውብ እንዲሆኑ በርካታ ሥራዎች መከናወናቸውን የጠቀሱት አቶ ጀማል የህብረተሰቡ ተሳትፎ አበረታች ውጤት ማስገኘቱንም ገልጸዋል።

በከተሞች ያለውን የመኖሪያ ቤት ችግር ለመፍታትና የቤት አቅርቦት በማህበር ለተደራጁ ዜጎች የመሥሪያ ቦታ መሰጠቱን ተናግረዋል።

የተጀመሩ ፕሮጀክቶች በፍጥነት እንዲጠናቀቁ በክልሉ መንግሥት በተቀመጠው አቅጣጫ መሠረት በአጭር ጊዜ ውስጥ ተጠናቀው ለህዝብ አገልግሎት እንዲውሉ ተደርጓል።

በከተማ ግብርና ሥራም በዓመት ሁለት ጊዜ እንዲመረት በተሰራው ሥራ 398 ሄክታር መሬት የለማ ሲሆን ከ39 ሺህ ኩንታል በላይ የተለያዩ ምርቶች ተሰብስበዋል።

በከተሞች መካከል የአገልግሎት አሰጣጥ ችግርን ለማሻሻል የሚያስችሉ ስራዎችና የልምድ ልውውጥ ተሞክሮ በማድረግ ለህብረተሰቡ ምቹ አገልግሎት ለመስጠት ጥረት መደረጉን ኃላፊው ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም