ቀጥታ፡

መንግስት የወሰደው የተናጠል ተኩስ አቁም እርምጃ ትክክለኛ ውሳኔ ነው - ምሁራን

አዳማ ሰኔ 24/2013/ኢዜአ/መንግስት የወሰደው የተናጠል ተኩስ አቁም እርምጃ የሀገርና የህዝብን ጉዳትና ጥቅም ያመዛዘነ ትክክለኛ ውሳኔ መሆኑን ምሁራን ገለጹ።

በኦሮሚያ አመራር አካዳሚ የዓለም አቀፍ ህግ ምሁርና የአመራር ልማት ዳይሬክተር አቶ ሳዲቅ አደም ለኢዜአ እንደገለጹት መንግስት የወሰደው የተናጠል ተኩስ አቁም እርምጃ  የሀገርና የህዝብን ጉዳትና ጥቅም ያመዛዘነ ትክክለኛ ውሳኔ ነው።

እርምጃው ሃላፊነትና ግዴታን ያስረከበበት ጭምር መሆኑን ተናግረዋል።

የተወሰደው እርምጃ ከህግ አንፃር ከማንም አካል ጋር በድርድር የተደረገ የተኩስ ማቆም ስምምነት ሳይሆን የተናጥል እርምጃ መሆኑን አመልክተዋል።

"ውሳኔው ዘርፈ ብዙና የጎላ ጠቀሜታ አለው" ያሉት አቶ ሳዲቅ ወቅቱ ክረምት በመሆኑ የትግራይ አርሶ አደር ወደ ልማት እንዲዞር ማገዙን ጠቅሰዋል።

በተጨማሪም ምዕራባዊያን ለሚያነሱት ወቀሳ ምላሽ የሚሰጥ መሆኑን አመልክተዋል።

አቶ ሳዲቅ አክለው  በመንግስት የተወሰደው እርምጃ የህዳሴ ግድብ ሁለተኛው ዙር የውሃ ሙሌት ለማከናወን ሃይሉን ወደ አንድ በማሰባሰብ የውስጥና የውጭ ጫናን ለመቋቋም የሚያስችል ሀገራዊ ዓላማና ግብ ያለው ውሳኔ መሆኑን ጠቅሰዋል።

አሸባሪው ቡድን  የኢትዮጵያ የሀገር መከላከያ ሠራዊት ተሸንፎ እንደወጣ  በማስመሰል የትግራይን ህዝብ ለማደናገር  እየተፍጨረጨረ መሆኑን ጠቁመው "ቡድኑ በማህበራዊ ሚዲያ ፕሮፓጋንዳና በምላስ ብቻ ያለ የደቀቀ ሃይል ነው " ሲሉ ገልጸውታል።

"መንግስት ከእንግዲህ በኋላ በቡድኑም ሆነ በተለያዩ ሀይሎች ለሚሰነዘሩ ለተለያዩ ክሶች ምክንያት የሚሆንበት ጉዳይ የለም" ብለዋል።

መንግስት የወሰደችው እርምጃ ለኢትዮጵያ፣ ለአፍሪካ ቀንድና ለዓለም ጭምር ትልቅ ፋይዳና ትርጉም ያለው መሆኑን አቶ ሳዲቅ አመልክተዋል።

"አሸባሪው ቡድን ለፉከራና ለቀረርቶ እንጂ በጭራሽ አቅም የለውም" ያሉት አቶ ሳዲቅ  "ቡድኑ አደብ ካልገዛና ትንኮሳ የሚፈፅም ከሆነ ብርቱ የሆነ የአፀፋ እርምጃ ሊወሰድበት ይገባል" ሲሉም ተናግረዋል።

"ቡድኑ በአካባቢው መንገድ የሚዘጋ፣ለጋሾችን የሚገድል፣የሰብዓዊ መብት ጥሰት የሚፈፅም አሸባሪ ሃይል በመሆኑ መንግስት ከእንግዲህ በአካባቢው ለሚፈጠረው ችግር ተጠያቂ አይሆንም" ብለዋል።

መንግስት የወሰደው እርምጃ  ሁሉም ሃላፊነትና ግዴታውን እንዲወስድ የሚጠይቅ ትክክለኛና ወቅታዊ ውሳኔ መሆኑን አስታውቀዋል።

"መንግስት በሀገር ሉዓላዊነት ላይ የተደቀነን አደጋ ለመቀልበስ የገባበት የህግ ማስከበር ዘመቻ ተልዕኮውን አሳክቷል" ያሉት ደግሞ የኦሮሚያ የህግ ጥናትና ምርምር ኢንስቲትዩት መምህርና ተመራማሪ አቶ ሽመልስ ሆርዶፋ ናቸው።

"የህግ ማስከበር ዘመቻው ትግራይን በሀይል ማስተዳደርና መውረር ሳይሆን ህገ መንግስታዊ ስርዓቱን ለማስከበር የተደረገ በመሆኑ በፌዴራል መንግስት የተወሰደው ውሳኔ ትክክለኛና ተገቢ ነው" ሲሉም አስታውቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም