ቀጥታ፡

“ለሃገር አሸናፊነት የተጣመሩ እጆች ስኬት!”

በእንግዳው ከፍያለው (ኢዜአ)

በብዙዎች ዘንድ የእንዴትነት ጥያቄ፣ ሃሳብና ስጋት ሲነሳበት የቆየው 6ኛው ሃገራዊ ምርጫ በሁሉም ቦታዎች ከተጠበቀው በላይ ህዝብ በመውጣት የተሳተፈበት ሆኖ አልፏል። ይሄ በአንዳንድ የሃገር ውስጥና የውጭ አካላት ቀደም ሲል ያልተተነበየ ቢሆንም በዛሬ ስማቸው ገዢውን ጨምሮ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ ህብረተሰቡና የምርጫ ታዛቢዎች ጭምር ሃገር ያሸነፈችበት ስለመሆኑም በተጨባጭ እየመሰከሩ ነው። “ነጻና ፍትሃዊ ምርጫ ማካሄድ አትችልም፤ ይባስ ብሎ አገሪቱ ወደ ግጭትና ብጥብጥ ልትገባ ትችላለች” ይሉ የነበሩ አካላትም ሆኖ ያዩት የወደፊቱን ተስፋ ያመላከተ የሃገር አሸናፊነትን የመሰከረ ሆኗል።በቅርብም በሩቅም ያሉ ታዛቢዎች ፣ዘጋቢዎችና ተንታኞች እስከ አሁን ያረጋገጡት ጉዳይ ይሄንኑ ነው።

ከምርጫው በፊት አንደንድ የውጭ መንግስታትና ድርጅቶች ያወጧቸው የነበሩ ሪፖርቶችም ሆኑ ምልከታዎች በአገር ውስጥ ካለው የጸረ-ሰላም ሃይሎች እንቅስቃሴ ጋር ተዳምሮ ህብረተሰቡ ምርጫውን እንደስጋት ማየቱን ባደረኳቸው ተደጋጋሚ ቃለ መጠይቆችም ጭምር ተረድቻለሁ። ምሁራኑም፣ ወጣቱም፣ ሴቱም ሆነ ሌላው የማህበረሰብ ክፍል ምርጫው ለአገራችን ስጋትን አርግዞ የመጣ እንደሆነ እስከማሰብ የደረሱም ታይተዋል።

ለነገሩ በእነሱ አይፈረድም ምርጫን ተከትሎ በሚከሰት ግጭት እንደ አፍሪካ ባሉ ታዳጊ አገራት ለዜጎች እልቂትና ንብረት መውደም ከመዳረግ ባሻገር ለተራዘመ ጦርነት የተጋለጡ መኖራቸው ሲታወስ “እባብ ያየ በልጥ በረየ” እንደሚባለው የአገራችን ህዝብም ደግሞ ደጋግሞ ቢሰጋ አይፈረድበትም። አስተያየት የሚሰጡኝ ሰዎች ስጋት ወደ እኔም ተጋብቶ ሂደቱን በጥንቃቄ መመርመር ጀምሬ ነበር። ከመርመር ባሻገር ከስራ ባልደረቦቼና ሌሎች ጓደኞቼ ጋርም አልፎ አልፎ አጀንዳውን በማንሳት ብዙ ጊዜ መከራከራችንን አስታውሳለሁ። 

የምርጫው እለት የተከሰተው ድርጊት ግን የውጭና የውስጥ ጠላቶችን ሴራ ያከሸፈ፣ ወዳጅ የሆኑ የውጭ አገራትን ያስደሰተ፣ የህዝቡን ስጋት ያስወገደ፣ የመንግስትን ዝግጅት ያስመሰገነ ሆኖ ማለፉም አሁን ላይ እየተነገረለት ይገኛል። መራጩ ህዝብ ራሱ ተሰላፊ፣ ስርዓት አስከባሪ፣ አስተባባሪና የኢትዮጵያውያን የመስተንግዶ ባህል የተንጸባረቀበት መሆኑን እኔ በተሰማራሁበት በደብረ ማርቆስ ከተማ በሚገኙ የምርጫ ጣቢያዎች ተዟዙሮ የሚመለከተው የፖለቲካ ፓርቲዎችና የጋዜጠኞች ቡድንም አረጋግጧል።

ጸሃዩና ዝናቡ ያልበገረው ህዝብ ለረጅም ሰዓታት እንደተሰለፈ ቅድሚያ ህጻን ልጅ የያዘች፣ ነፍሰ ጡር፣ አቅመ ደካማና የአካል ጉዳት ያለባቸው የህብረተሰብ ክፍሎች በመስጠት መርጠው እንዲሄዱ በራሱ ተነሳሽነት ሲያስተናግድ ማየት ምን ያህል የሞራል ልዕልናና የመንፈስ ጽናት የተጎናጸፈ ህዝብ እንደሆነ በቀላሉ መረዳት አያዳግትም። ከተለያዩ መገናኛ ብዙሃን የተወጣጣው የጋዜጠኞች ቡድን ከክልሉ ማዕከል ባህርዳር ዕለተ ምርጫውን ቀድሞ መገኘቱም ዋነኛ መነሻው ይሄንኑ ታሪክ ለህዝብ ለማሳየትና ለመሰነድ ነበር።

በምርጫው ዋዜማ ጭምር አስተያየት የሚሰጡ ሰዎች ያላቸውን ምኞት ተስፋና ስጋት ይገልጹ ነበር። ሰኔ 14/2013 በወጉ ሳይነጋ ተነስተን በተዘዋወርንባቸው የደብረ ማርቆስ ከተማ ቀበሌ 03፣ 04፣ 05፣ 07፣ እና በሌሎች አካባቢዎች የሚገኙ የምርጫ ጣቢያዎች ህዝቡ በነቂስ ወጥቶ መሰለፉን ተመልክተናል። በሰፊ ትዕግስት ወረፋውን እየጠበቀ ብርድ፣ዝናብ ጸሐይ ሳይል ድምጹን ሲሰጥ የዋለው መራጭን ሁኔታ ስንከታተል ውለን ማታ ላይ እኔ ካለሁበት ደብረ ማርቆስ በብዙ ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የሚገኝ አንድ የስራ ባልደረባዬ ደወለ፤ ስልኩን እንዳነሳሁለት በድካም ስሜት፣ “ሃሎ ምርጫው እንዴት ነው?” የሚል ጥያቄውን አቀረበልኝ 

“በኛ ሰላም ነው፤ ህዝቡ በነቂስ ወጥቶ በሰላም መርጧል። አሁን ሰዓቱ እየመሸ ቢሆንም መራጩ ግን ወደ ምርጫ ጣቢያ በመምጣት እየተሰለፈ ነው” አልኩት።

“በናንተስ?” የሚል ጥያቄም አስከተልኩ፤

እርሱም “የሚገርም ነው በኛም መራጩ ህዝብ በስርዓት ይሰለፋል፤ ተራው ሲደርሰው በነጻነት መርጦ ይሄዳል፤በመላ ኢትዮጵያ ያለው ህዝብ ተመካክሮ፣ ተነጋግሮና ተወያይቶ ውሳኔ የደረሰበት እኮ ነው የሚመስለው የድርጊቱ ተመሳሳይነት” አለኝ። በአገላለጹም ተስማማሁ።

እንደሚታወቀው አንዳንድ የውጭ መንግስታትና ድርጅቶች ምርጫውን ለማሰናከል ያላደረጉት ጥረት የለም። በቀጥታ ጣልቃ የመግባት አባዜም የታየው በዚህ ምርጫ ወቅት ነው። ምርጫው በሰላም መጠናቀቁ እንግዲህ ለነዚህኞቹ የመልስ ምት መሆኑን የገለጸው ባለደረባዬም “ኢትዮጵያ ያሸነፈችበት ምርጫ ነው” በሚል ክስተቱን ገልጾታል።

የኢትዮጵያ ማሸነፍ ጉዳይ በአዕምሮዬ ደጋግሞ ተመላለሰ። አባቶቻችን ሃገራቸው የሚገባትን ክብርና ከፍታ ለማጎናጸፍ በሚከፍሉት መስዋዕትነት ምክንያት ድል ብርቃቸው አልነበረም። በተለያየ ጊዜ በሃገር ላይ የተቃጡ ወረራዎችንና ጥቃቶችን በብቃት መልሰዋል።ግብጽን በተደጋጋሚ አሸንፈዋል። ጣሊያንን አድዋ ላይ አይቀጡ ቅጣት መቅጣታቸውን ከታሪክ ተምሬያለሁ፤ አንብቤያለሁ። ጣሊያንም ሆነች ግብጽ የተለያዩ አገራት ናቸው። ሙከራቸው ግን በአባቶች ንቁ መከላከልና ሃገራዊ ወኔ ሊሳካ አልቻለም የሚያሳፍር ታሪክ ከመጻፍ ውጭ።

በአድዋ ድል ጣሊያን ብቻ ሳትሆን የተሸነፈችው የነጮች የበላይነት አስተሳሰብ መገለጫ የነበረው ጥቁሮችን የመግዛት ህልማቸውም ጭምር ነበር። ኢትዮጵያ በታሪኳ የተለያዩ የቅርብም የሩቅም ጠላቶች ገጥመዋት ሳትንበረከክ አልፋዋለች። ዜጎችም በተባበረ ክንድ ሃገር ለመጠበቅ የሚያደርጉት ጥረትና ድካም አሳፍሯቸው አያውቅም።ዛሬ ላይ ደግሞ ሁሉም በአንድ ሃሳብ የተነጋገሩበትና የተግባቡበትን የዘንድሮውን ምርጫ በማበላሸት ሃገር የገጠማትን ፈተና ለማባባስ እንደ ታላቁ የህዳሴ ግድብ ያሉ ግዙፍ ፕሮጀክቶችን ለማስቆም ያላደረጉት ጥረት እንደሌለ አየታየ ነው። ህዝብና መንግስትም ከማውራት መስራት በሚለው መርህ ጥርሳቸውን ነክሰው የጀመሯቸውን ፕሮጀክቶች ዳር ለማድረስ ርብርብ እያደረጉ ባሉበት ጊዜ ላይ ይሄን ምርጫ በሰላማዊ መንገድ ማጠናቀቅ ታላቅ ድል ነው።

ኢትዮጵያውያን የተለየ የስነ ልቦና፣ ስብእና፣ በራስ የመተማመን፣ የነጻነት… ስሜት እንዳላቸውና ይህንንም ከጥንት አባቶቻቸው የወረሱት መሆኑን በታሪክ ድርሳናት ተሰንዶ ይገኛል። በዚች አገር ላይ መከራው ቢበዛም፣ ፈተናው ቢጠናም፣ አሜካላው ቢዘራም ህዝቦቿ አንድነትና ጽናት የገጠማትን ችግር በህዝቦቿ አንድነት መወጣት የምትችልበት የመንፈስ ጥንካሬ እንዳላት በ6ኛው አገራዊ ምርጫ ማረጋገጥ ተችሏል። በምስራቅ ጎጃም ዞን ከሚወዳደሩት ሰባት ፓርቲዎች ውስጥ የብልጽግና፣ ኢዜማና መኢአድ ተወካዮች በጋራ የምርጫ ጣቢያዎቹን ተዘዋውረው በመጎብኘት ወዲያው በምርጫው እለት ነጻና ፍትሀዊ ምርጫ መሆኑን ማረጋገጣቸውን በወቅቱ በዘገባ ለህዝብ ጆሮ ማድረሳችንም ይታወሳል።

በደብረ ማረቆስ ከተማ የኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትህ/ኢዜማ/ ተወካይ አቶ ሰሎሞን ጉልበት በምርጫው እለት “የምርጫው ሰላማዊ፣ ፍትሃዊና ዴሞክራሲያዊ ሆኖ አግኝተነዋል” ብለዋል። ይህ ጅምር እንቅስቃሴ በቀጣይ ኢትዮጵያውያን ሀገራቸውን ወደ ዴሞክራሲ ከፍታ ለማሸጋገር የሚያስችል የተሟላ አቅም እንዳላቸው ማሳያ ነው” ብለውታል።

ውጤቱ ምንም ይሁን ምን መራጩ ህዝብ ያለምንም ተጽእኖ በነጻነት ድምጹን ለሚፈልገው የፖለቲካ ፓርቲ ያለምንም ጫና መስጠቱ የአገራችንን ዘላቂ ሰላም በሚያረጋግጥ የውጭና የውስጥ ሃይሎችን እኩይ ድርጊት ለማክሸፍ ፋይዳው የጎላ እንደሚሆንም ጠቅሰዋል። ኢዜማም እስከ አሁን ከፖለቲካው ስራ ይልቅ ኢትዮጵያ ከነሙሉ ክብሯና ሉአላዊነቷ ተከብራ እንድትቀጥል አተኩሮ መስራቱን አመልክተዋል። ህዝቦች በዜግነታቸው ተከብረው የሚኖሩባትን አገር ለመገንባት ከመንግስት ጎን በመሰለፍ በቁርጠኝነት እንደሚሰሩም ተወካዩ አረጋግጠዋል።

“የዘንድሮው ምርጫ በጠላትነት ሲተያዩ የነበሩት የተፎካካሪና የገዥው ፓርቲዎች በጋራ በመሆን ተባብረው መስራት የጀመሩበት የመጀመሪያው ምዕራፍ ነው” ሲሉ ያረጋገጡት ደግሞ የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት/መኢአድ/ ተወካይ አቶ ብርሃኑ ማናየ ነበሩ። “በደብረ ማርቆስ ከተማ በሚገኙ የምርጫ ጣቢያዎች ተፎካካሪ ፓርቲዎች በአንድ ላይ በመሆን ተዘዋውረን የድምጽ አሰጣጥ ሂደቱን እየተከታተልን ነው። እስከ አሁን የጎላ ችግር አላገጠመንም” ያሉት ተወካዩ ችግሮች አሉ ቢባል እንኳን በአንድ ላይ በመነጋገርና በመፍታት ምርጫው ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ የበኩላቸውን እንደተወጡም አስረድተዋል።

የደብረ ማርቆስ ከተማ ከንቲባ አቶ ይትባረክ አወቀም ይሔንኑ ሃሳብ ይጋራሉ። ካለፉት አምስት ተከታታይ ምርጫዎች ትምህርት በመውሰድ በሰኔ 14/2013 ዓ.ም የተከሄደውን ምርጫ ሰላማዊ፣ ፍትሃዊና በህዝብ ዘንድ ተአማኒ ለማድረግ ከቅድመ ምርጫ ጀምሮ ያለሰለሰ ጥረት መደረጉን ገልጸዋል።

በጸጥታ አካላት፣ በምርጫ አስፈጻሚዎች፣ ታዛቢዎችና ሌሎች አካላት ላይ ምርጫውን በስኬት ለማጠናቀቅ የሚያስችል ተከታታይ ስራ ተሰርቷል። ይህም ያለምንም ተጽዕኖ ሁሉም የየድርሻውን እንዲወጣ ተደርጓል ብለዋል።

በዚህ ምርጫ ከየትኛውም የፖለቲካ ፓርቲ ይልቅ አሸናፊ የሆነችው የኢትዮጵያ ድል ቀድሞ ተሰምቷል። እርግጥ ነው። ይሄ ጉዳይ የብዙዎችን ቀልብ የሳበ ውጤቱም ተናፋቂ ሆኖ መቆየቱም ይታወቃል። ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የተጠቃለለ ውጤት ከማውጣቱ በፊትም ቢሆን እየታየ ያለው የተፎካካሪዎች ድባብ በበጎ የሚታይ ነው።

ህዝብ የሰጠው ድምጽ ተቆጥሮ ይፋ ሲደረግም ሁሉም አካላት የተገኘውን ውጤት መሰረት ባደረገ መልኩ ሃገርን በሚጠቅሙ ጉዳዮች ላይ ተባብሮ መስራትን ቅድሚያ ትኩረታቸው እንዲያደርጉ ይጠበቃል። ሃገር እንድታሸንፍ ሁሉም አካላት በፈጠሩት የጋራ ጥምረት የተገኘው ውጤት በቀጣይም ሊያጋጥሙ የሚችሉ ፈተናዎችን በቀላሉ ለማለፍ እንደሚቻል ያመላከተ እንደመሆኑ ሃገርን የማስቀደሙ ጉዳይም መጠናከር ይኖርበታል።  

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም