ጎረቤት አገራት ከኢትዮጵያ ለሚቀርቡላቸው ችግኞች ለተከላ የሚመች የጊዜ ሰሌዳ አስቀምጠዋል - ኢዜአ አማርኛ
ጎረቤት አገራት ከኢትዮጵያ ለሚቀርቡላቸው ችግኞች ለተከላ የሚመች የጊዜ ሰሌዳ አስቀምጠዋል
አዲስ አበባ፤ ሰኔ 24/2013 (ኢዜአ) ከኢትዮጵያ ለሚቀርቡላቸው ችግኞች ጎረቤት አገራት ለተከላ የሚመች የጊዜ ሰሌዳ ማስቀመጣቸውን የአካባቢ ደንና አየር ንብረት ኮሚሽን ገለጸ።
ሩዋንዳና ዩጋንዳም ኢትዮጵያ የችግኝ ድጋፍ እንድታደርግላቸው ጠይቀዋል።
ኢትዮጵያ በጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ ተነሳሽነት ከሦስት ዓመት በፊት የአረንጓዴ አሻራ መርሃ-ግብርን መጀመሯ ይታወሳል።
በኢትዮጵያ ባለፉት ሶሰት ዓመታት የተጠናከረ የአረንጓደ አሻራ መርሃ ግብር እየተከናወነ ይገኛል።
ዘንድሮም ‹‹ኢትዮጵያን እናልብስ›› በሚል መሪ ሃሳብ ብሄራዊ የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር የተጀመረ ሲሆን 6 ቢሊዮን ቸግኞችን ለመትከል ታቅዷል።
ለጎረቤት አገራት ደግሞ አንድ ቢሊዮን ችግኞችን ለማድረስ የታሰበ ሲሆን አገራቱ ችግኞቹን ተቀብለው ለመትከል አመቺ ወቅት እየጠበቁ መሆኑን የአካባቢ ደንና አየር ንብረት ኮሚሽን ኮሚሽነር ፕሮፌሰር ፍቃዱ በየነ በተለይ ለኢዜአ ገልጸዋል።
ዓለምን እየፈተነ ያለው የአየር ንብረት ለውጥ አገራት በተናጠል በሚያደርጉት ጥረት ብቻ ሊገታ ስለማይችል የትብብር ልማት ወሳኝ መሆኑን ገልጸዋል።
ታዳጊ አገራት ምንም እንኳን ለአየር ንብረት መዛባት ያላቸው ሚና ዝቅተኛ ቢሆንም የችግሩ ዋነኛ ገፈት ቀማሾች በመሆናቸው ለዘርፉ ልማት ትኩረት አድርገው መስራት ይኖርባቸዋል ነው ያሉት።
ለዚህም ኢትዮጵያ በቁርጠኝነት እየሰራች መሆኑንና ለአካባቢው አገራት ችግኞችን ተደራሽ ለማድረግ የያዘችው እቅድም በአርአያነት የሚጠቀስ መሆኑን ጠቅሰዋል።
ኢትዮጵያ ዘንድሮ ለደቡብ ሱዳን 91 ሚሊዮን፣ ለሱዳን 356 ሚሊዮን፣ ለኤርትራ 29 ሚሊዮን፣ ለጅቡቲ 9 ሚሊዮን፣ ለሶማሊያ 129 ሚሊዮን እንዲሁም ለኬኒያ 380 ሚሊዮን ችግኞችን ለማድረስ ተዘጋጅታለች።
የችግኝ ድጋፉ በአፍሪካ ቀንድ ከሚገኙ አገሮች በተጨማሪ ሩዋንዳና ዩጋንዳ ባሳዩት ፍላጎት መሠረት ድጋፍ እንደሚደረግላቸውም ኮሚሽነሩ ገልጸዋል።
አገራቱ ችግኝ መትከል ብቻ ሳይሆን ባለቤት ሰጥተው ችግኙ እስኪጸድቅ አስፈላጊውን እንክብካቤ እንዲያደርጉ በየአገሮቹ ከሚገኙት የኢትዮጵያ ኤምባሲዎች ጋር ቅድመ- ዝግጅት ተደርጓል ብለዋል።
በኢትዮጵያ በ2013 ዓ.ም.በተከናወነ ሳይንሳዊ የሳተላይት ቆጠራ በ2007 ዓ. ም. በ15 ነጥብ 5 በመቶ የነበረው የደን ሽፋን ወደ 17 ነጥብ 2 በመቶ ከፍ ብሏል።
ባለፉት ሁለት ዓመታት በተከናወነው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ-ግብር በመላ ኢትዮጵያ የተለያየ ዝርያ ያላቸው 9 ቢሊየን አገር በቀል ችግኞች ተተክለዋል።