ኢትዮጵያና ሉክሰምበርግ ተደራራቢ ታክስን ማስቀረት የሚያስችላቸውን ስምምነት ተፈራረሙ - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያና ሉክሰምበርግ ተደራራቢ ታክስን ማስቀረት የሚያስችላቸውን ስምምነት ተፈራረሙ
ሰኔ 23/2013 (ኢዜአ) ኢትዮጵያና ሉክሰምበርግ ተደራራቢ ታክስን ማስቀረትና በታክስ ጉዳዮች ላይ በጋራ መስራት የሚያስችላቸውን ስምምነት ተፈራረሙ።
በሉክሰምበርግ ከተማ የተካሄደውን ስምምነት በቤልጂየም፣ በሉክሰምበርግና በአውሮፓ ሕብረት ተቋማት የኢትዮጵያ አምባሳደር ሂሩት ዘመነና የሉክሰምበርግ የፋይናንስ ሚኒስትር ፒዬር ግራሜኒያ ተፈራርመዋል።
ስምምነቱ በሁለቱ ሀገራት መካከል ባለው የገቢና የካፒታል ወጪ ላይ የሚጣሉ ተደራራቢ ታክስ የሚያስቀር፤ እንዲሁም ሀገራቱ ታክስ ስወራና ማጭበርበርን በጋራ መከላከል የሚያስችላቸው ነው።
የተፈረመው ስምምነት ኢትዮጵያና ሉክሰምበርግ በኢኮኖሚው መስክ ያላቸውን ግንኙነት ይበልጥ የሚያሳድግና በታክስ ጉዳዮች ላይም ያላቸውን ትብብር እንደሚያሳድግ በብራሰልስ የሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ ለኢዜአ በላከው መግለጫ አስታውቋል።
በስምምነቱ ወቅት ሁለቱ አገራት የሁለትዮሽ ግንኙነታቸውን በሚያጠናከሩበት ሁኔታና በኢትዮጵያ ወቅታዊ ሁኔታ ዙሪያ የሀገራቱ ባለስልጣናት ሐሳብ መለዋወጣቸው ተነግሯል።
ኢትዮጵያና ሉክሰምበርግ አንድ ክፍለ ዘመን የተጠጋ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት እንዳላቸው መረጃዎች ያመለክታሉ።