ኢንስቲትዩቱ ከሦስት መቶ ሺህ ብር በላይ ግምት ያላቸውን መጽሐፎች ለጠቅላይ ፍርድ ቤት በስጦታ አበረከተ

66

ሰኔ 23/2021 (ኢዜአ) የፌዴራል የፍትህና የሕግ ምርምር ኢንስቲትዩት ከሦስት መቶ ሺህ ብር በላይ ግምት ያላቸው የሕግ ጥናትና ምርምር መጽሐፎች ለፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት በስጦታ አበረከተ።

ኢንስቲትዩቱ 2ሺህ 100 የሚሆኑ ስድስት የሕግ መድብሎች እና 120 የሚደርሱ የነጋሪት ጋዜጣ አሥር ጥራዞችን ነው በስጦታ ያበረከተው። 

የተበረከቱት መጽሐፎችና የጋዜጣ ጥራዞች በተለያዩ ዓመታት በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ጸድቀው የታተሙ ናቸው።

የፌዴራል የፍትህና የሕግ ምርምር ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር አምባሳደር ደግፌ ቡላ በዚህን ወቅት ኢንስቲትዩቱ ሙያዊ ሥልጠናን ከመስጠት ባሻገር የህትመት ውጤቶችን ተደራሽ እንደሚያደርግ ተናግረዋል።

የኢንስቲትዩት ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ምትኩ ማዳ በበኩላቸው የተበረከቱት መጽሐፎች የፍትሕ አካላትን ሙያዊ አቅም በመገንባት ረገድ ፋይዳቸው የጎላ መሆኑን ገልጸዋል።

የህትመት ውጤቶቹ የተበረከቱበት ዋነኛ ዓላማ የፍትሕ ሥርዓቱን ብቁና ዘመናዊ ለማድረግ እንዲሁም መልካም አስተዳደርን ለማስፈን የሚደረገውን ጥረት ለመደገፍ መሆኑን ነው የተናገሩት።

ኢንስትቲዩቱ በተጨማሪ ከ30 በላይ ለሚሆኑ የሕግ ትምህርት ቤቶችና ተቋማት የሀገሪቱን የሕግ መድብሎች፣ የነጋሪት ጋዜጣ ጥራዞችን እና ማየት ለተሳናቸው ዜጎች የተዘጋጁ የሕግ መድብሎችን ማበርከቱንም ተናግረዋል።

ድጋፉ ለፍርድ ቤቱ የአቅም ግብዓት በመሆን ከፍተኛ ጥቅም አለው ያሉት ደግሞ የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ምክትል ፕሬዝዳንት አቶ ሰለሞን አረዳ ናቸው።

ኢንስቲትዩቱ የዳኝነት ሥነ-ሥርዓቶችን ለማሻሻል በሚደረጉ ጥረቶችን እየደገፈ መሆኑን ጠቅሰዋል፤ ለተደረገው ድጋፍ ምስጋና አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም