በትግራይ ክልል በመንግስት የተደረገው የተናጠል የተኩስ አቁም ውሳኔ ለሰብዓዊነት ቅድሚያ በመስጠት ነው-- የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር - ኢዜአ አማርኛ
በትግራይ ክልል በመንግስት የተደረገው የተናጠል የተኩስ አቁም ውሳኔ ለሰብዓዊነት ቅድሚያ በመስጠት ነው-- የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር
አዲስ አበባ፣ ሰኔ 23/2013 (ኢዜአ) በትግራይ ክልል በመንግስት የተደረገው የተናጠል የተኩስ አቁም ውሳኔ ለሰብዓዊነት ቅድሚያ በመስጠት መሆኑን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ገለጸ።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን እና የመከላከያ ሰራዊት ግንባታ ስራዎች ዋና አስተባባሪ ሌተናል ጀነራል ባጫ ደበሌ በወቅታዊ ጉዳይ ላይ በጋራ መግለጫ ሰጥተዋል።
በትግራይ ክልል የተኩስ አቁም ስምምነት ውሳኔ ላይ ፖለቲካዊ አና ወታደራዊ እንድምታው ላይ በማተኮር ማብራሪያ ሰጥተዋለ።
በትግራይ ክልል በመንግስት የተደረገው የተናጠል የተኩስ አቁም ውሳኔ ለሰብዓዊነት ቅድሚያ የሰጠ መሆኑን አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን ገልጸዋል።
በክልሉ ችግሩ እንዳይከሰት መንግስት ቀደም ብሎ በውይይት እንዲፈታ ጥረት ቢያደርግም በህወሃት በኩል ተቀባይነት ማጣቱን አስታውስዋል።
በሃይማኖት አባቶችና በታዋቂ ሰዎች ለውይይትና ሰላም ይደረጉ የነበሩ ጥረቶችም በዚሁ ሃይል መገፋቱን ተናግረዋል።
እነዚህ ሁሉ ጥረቶች እየተደረጉ በነበሩበት አጋጣሚ የህወሃት ቡድን በአገር ጠባቂው የአገር መከላከያ ሰራዊት ላይ ጥቃት በመፈፀም የአገር ክህደት መፈፀሙን አስረድተዋል።
በዚህም መንግስት አገር የማዳን አስገዳጅ ሁኔታ ስላጋጠመው ወደ ህግ ማስከበር መግባቱን ገልጸዋል።
መንግስት ህግ ማስከበሩን በ3 ሳምንታት ውስጥ ማጠናቀቅ ቢችልም አሸባሪው ሃይል መደበኛ የአርሶ አደር ልብስ ለብሶ ወደ ሽምቅ ውጊያ በመግባት ላለፉት 8 ወራት አካባቢውን ለችግር መዳረጉን ነው የገለፁት አምባሳደር ሬድዋን።
ለተፈጠረው ቀውስ የመከላከያ ወጪን ሳይጨምር መንግስት እስካሁን ከ100 ቢሊዮን ብር በላይ ወጪ ማድረጉን ጠቅሰዋል።
በክልሉ ያለው ችግር ተባብሶ ቀጥሎ ኢትዮጵያ እንድትዳከም የሚሹ አካላት በመኖራቸው ለሰብአዊነት ቅድሚያ በመስጠት የመከላከያ ሃይል አካባቢውን ለቅቆ መውጣቱን ነው የተናገሩት።
የትግራይ ክልል አርሶ አደሮች የመኸሩ ጊዜ ሳያልፍ ወደ እርሻ እንዲገቡ ታቅዶ የሰብዓዊነት ውሳኔ መሰጠቱንም ነው አምባሳደር ሬድዋን ያስረዱት።
ከዚህ በኋላ በትግራይ ክልል ለሚፈጠረው ችግር ሁሉ ተጠያቂው ሽብርተኛው ቡድን መሆኑንም ነው የተናገሩት።
የመከላከያ ሰራዊት ግንባታ ስራዎች ዋና አስተባባሪ ሌተናል ጀነራል ባጫ ደበሌ፤ ሽብርተኛው ህወሐት የማይመራት ኢትዮጵያ እንዳትኖር አቅዶ ሲሰራ መቆየቱን ገልጸዋል።
አገር ለማፍረስ ተዘጋጅቶ የነበረውን የህወሃት ጁንታ መከላከያ ሰራዊት በአጭር ጊዜ ድል በማድረግ በርካታ ስራዎችን ሲያከናውን መቆየቱን አስረድተዋል።
አሸባሪው ቡድን ከተሸነፈ በኋላ ወደ ሽምቅና ሽፍትነት በመግባት በዜጎች ላይ የተለያዩ ጉዳቶችን ሲያደርስ መቆየቱን ጠቅሰዋል።
የሀገር መከላከያ ሰራዊት በመቀሌ በነበረው ስምሪት አሸባሪው ከእስር ቤት የፈታቸውን በ10 ሺዎች የሚቆጠሩ እስረኞች ህዝብ ላይ ጉዳት እንዳያደርሱ ጥበቃ ሲያደርግ መቆየቱንም ነው የገለፁት።
አሁን ላይ ግን መቀሌን መልቀቅ ከስትራቴጂክ ጠቀሜታ አንፃር ከተማዋን ለቅቀን ወጥተናል ብለዋል።
የህወሃት አሸባሪ ቡድን አሁን ላይ የኢትዮጵያ ስጋት አይደለም ሲሉም ተናግረዋል።