ቀጥታ፡

ሳዑዲ አረቢያ አዲስ ብሔራዊ የአየር መንገድ ልትገነባ ነው

ሰኔ 23 ቀን 2013 (ኢዜአ) ሳዑዲ አረቢያ የዓለም አየር መንገድ ዘርፍ ማዕከል የሚያደርጋትን አዲስ አየር መንገድ ለመገንባት ማቀዷን የሀገሪቱ ንጉስ ሞሀመድ ቢን ሳልማን ገልጸዋል፡፡

አዲሱ ፕሮጀክት ሀገሪቱን የዓለም የሎጂስቲክስ ማዕከል ማድረግ የሚያስችሉ የወደብ ግንባታ፣ የባቡር እና የመንገድ ትስስርን ያሳድጋል ተብሏል።

ይህም አሁን ያለውን የሀገሪቱን ዓመታዊ ጥቅል ዕድገት ከ6 በመቶ ወደ 10 በመቶ ማሳደግ በሚያስችል መልኩ የሚከናወን መሆኑም አልጄዚራ ዘግቧል።

በዓለም የአየር በረራ አገልግሎት ዘርፍ አምስተኛ ደረጃ ላይ የምትቀመጠው ሳዑዲ አረቢያ አሁን ለመገንባት ያሰበችው አዲሱ አየር መንገድ በሀገሪቱ ሁለተኛው ግዙፍ አየር መንገድ እንደሚሆን ታምኖበታል፡፡

ሳዑዲ አሁን የምትገነባው አየር መንገድ ሀገሪቱ ከነዳጅ ገቢ በተጨማሪ እኤአ እስከ 2030 ባለው ጊዜ ድረስ 12 ቢሊየን ዶላር ገቢ እንደሚያስገኝ በዚህም ሀገሪቱን በአረቡ ዓለም የግዙፍ ኢኮኖሚ ባለቤትና ታላቅ እንደሚያደርጋት ተገልጿል፡፡

ይህ ዕቅድ ተግባራዊ ሲሆን ቀደም ሲል የነበረውን የበረራ መዳረሻ ቁጥር እስከ 250 ያደርሰዋል ተብሏል።

ይህም ይሰጥ የነበረውን የጭነት አገልግሎት በእጥፍ በማሳደግ ከ4 ነጥብ 5 ሚሊየን ቶን በላይ በማድረስ በሀገሪቱ ገቢ በማስገባት የሚታወቁት ቱሪዝም፣ ሀጅ እና ኡምራ ዘርፎች ዕቅዳቸውን እውን እንዲያደርጉ የሚያግዝ መሆኑን ንጉስ ሳልማን መናገራቸውን ዘገባው አስታውሷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም