ቀጥታ፡

አሜሪካና የተባበሩት አረብ ኢሚሬቶች የኢትዮጵያ የተናጥል ተኩስ አቁም ጥሪ አበረታች እርምጃ መሆኑን ገለጹ

ሰኔ 23 ቀን 2013 (ኢዜአ) የአሜሪካና የተባበሩት አረብ ኢሚሬቶች ኢትዮጵያ ላደረገችው የተናጥል ተኩስ አቁም ጥሪ አበረታች እርምጃ መሆኑን ገልጸዋል።
የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ባወጣው መግለጫ እንዳስታወቀው የተኩስ አቁም ሂደቱ ግጭትን ለማስቆምና የሰብአዊ ድጋፍ ለሚሹ ወገኖች እንዲደርስ ለማድረግ መሰረት ያለው ነው።
የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት እና የግዛት አንድነት ለመጠበቅ እንዲሁም በትግራይ መረጋጋት እንዲመጣ ሁሉም አካላት የበኩላቸውን አስተዋጽኦ እንዲያደርጉ አሜሪካ ጥሪ አቅርባለች፡፡
ሁሉም ወገኖች ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ ህግን በጥብቅ እንዲያከብሩ እና የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች እና በደሎች ተጠያቂነትን ለማስፈን እንደሚረዳ በመግለጫው ተጠቅሷል፡፡
አሜሪካ በትግራይ ድጋፍ ለሚያስፈልጋቸው ወገኖች ድጋፍ ለማድረግ ከሌሎች ዓለም አቀፍ አጋሮች ጋር በትብበር ለመስራት ዝግጁነት እንዳላት ተገልጿል፡፡
የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች የውጭ ጉዳይ እና ዓለም አቀፍ ትብብር መስሪያ ቤት በበኩሉ ባወጣው መግለጫ በትግራይ ተኩስ አቁም በኢትዮጵያ መንግስት በኩል መታወጁ የሚደገፍ ሃሳብ መሆኑን አስታውቋል፡፡
የተባበሩት አረብ ኤሜሬቶች በኢትዮጵያ ትግራይ ክልል የተኩስ አቁም ስምምነቱን በደስታ እንደተቀበለችው ገልጻ፤ ውሳኔው ለችግሮች መፍትሄ እንዲኖር የሚያደርግ መሆኑንም አስታውቃለች፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም