መገናኛ ብዙኃን ብሔራዊ ደህንነትን ጥያቄ ውስጥ ሳያስገቡ የሙያ ስነ-ምግባር ላይ ተመርኩዘው ሊሰሩ እንደሚገባ ተገለፀ - ኢዜአ አማርኛ
መገናኛ ብዙኃን ብሔራዊ ደህንነትን ጥያቄ ውስጥ ሳያስገቡ የሙያ ስነ-ምግባር ላይ ተመርኩዘው ሊሰሩ እንደሚገባ ተገለፀ
አዲስ አበባ፤ ሰኔ 22 ቀን 2013 (ኢዜአ) መገናኛ ብዙኃን ብሔራዊ ደህንነትን ጥያቄ ውስጥ ሳያስገቡ የሙያ ስነ-ምግባር ላይ ተመርኩዘው ሊሰሩ እንደሚገባ ተገለፀ።
አንጋፋ ጋዜጠኞች በኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን የሚታዩ ችግሮች እና ቀጣይ የመፍትሔ አቅጣጫዎች ላይ ውይይት አካሂዱ።
የውይይት መድረኩ በኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን የተዘጋጀ ሲሆን፤ አንጋፋ ጋዜጠኞቹ ከእውቀትና ከልምዳቸው አኳያ ሐሳብ እንዲያካፍሉ ዓላማ አድርጎ የተዘጋጀ ነው።
በውይይቱ ወቅት በመገናኛ ብዙኃን የሚስተዋሉ ችግሮች የተነሱ ሲሆን፤ 'መገናኛ ብዙኃን በምን አቅጣጫ መመራት አለባቸው' የሚሉ የመፍትሄ አቅጣጫዎችም ተመላክተዋል።
ከ50 ዓመታት በላይ በጋዜጠኝነት ሙያ ልምድ ያካበቱት አቶ ማዕረጉ በዛብህ በሰጡት አስተያየት፤ የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ለዓለም አቀፍ ማህበረሰብ ተደራሽ አለመሆናቸውን ገልጸዋል።
የባለሙያው ብቃት ማነስና የሙያ ጥራት መጓደል፣ ከቋንቋ አጠቃቀም አኳያ ችግሮች እንደሚስተዋሉ ተናግረዋል።
የሸገር ኤፍ ኤም ዋና ሥራ አስኪያጅ ወይዘሮ መዓዛ ብሩ በበኩላቸው፤ የመገናኛ ብዙኃን ነጻነትን ለማስከበር ህጎች ቢሻሻሉም መገናኛ ብዙሃኑ ግን በተለያዩ አካላት ተጽዕኖ ውስጥ የወደቁ መሆናቸውን ነው ያወሱት።
መረጃ የማግኘት ችግር፣ የጋዜጠኝነትና የተሟጋችነት ሚና መደበላለቅ፣ ከሙያ ስነ-ምግባር፣ ከመገናኛ ብዙሃን ባለቤትነት ተጽዕኖ፣ ከገለልተኝነት እና ወገንተኝነት እንዲሁም ከባለሙያው እውቀት ክፍተት ጋር የተያያዙ ችግሮች እንደሚስተዋሉ ተናግረዋል።
ደራሲ አቶ ጌታቸው በለጠ ለኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ወቅት የወለደው ተግዳሮት መካከል አንዱ መጽሀፍትን ማንበብ በመተው ተገቢ ባልሆነ መንገድ ቴክኖሎጂ ላይ ጊዜውን ማጥፋቱ ነው።
ሌላኛው አንጋፋ ጋዜጠኛ አቶ ኃይሉ ወልደጻዲቅ በበኩላቸው እንደገለጹት፤ አሁን ላይ በብዛት በመገናኛ ብዙኃን የሚስተዋለው የተሟጋችና የፕሮፓጋንዳ ዓይነት ዝንባሌዎች መገታት አለባቸው።
አገር ከሌለ መገናኛ ብዙሃን የሌሉ በመሆኑ የአገር ሰላም፣ ሉዓላዊነትና ደህንነትን በማሰቀደም በአንድ ዘርፍ ላይ የካበተ ልምድ ያላቸው ጋዜጠኞች እንዲኖሩ ማድረግ እነደሚያስፈልግ ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ምክር ቤት ሥራ አስፈጻሚ አቶ ታምራት ኃይሉ፤ በአሁኑ ወቅት "ማነው ጋዜጠኛ?" የሚለው ነገር መገናኛ ብዙኃንን ጥያቄ ውስጥ እንዲገቡ ማድረጉን ነው የገለጹት።
የሙያ ነጻነት መጓደልና የስነ-ምግባር ችግር፣ የማህበራዊ ሚዲያ ተጽዕኖ፣ የጋዜጠኛና የአንቂነት ሙያ መደበላለቅ ለዘርፉ ሳንካ እየሆኑ መምጣታቸውን ነው የተናገሩት።
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የጋዜጠኝነት ትምህርት ቤት ረዳት ፕሮፌሰር አማኑኤል አብዲሳ በኢትዮጵያ "የመገናኛ ብዙኃን የትግል ሜዳ እየሆኑ መጥተዋል" ብለዋል። ይህም የግለሰብ ሐሳብንና ፈቃድን ለማገልገል በባለቤትነት ላይ ተመስርተው መስራታቸው የትግሉ መገለጫ ነው።
የሙያው ስነ-ምግባር ለሁሉም የሚሰራ በመሆኑ አገራዊ ጥቅምንና ደህንነትን ጥያቄ ውስጥ ባላስገባ መልኩ ሙያውን በትክክል ስነ-ምግባርን ጠብቆ መሥራት እንደሚገባ ነው የገለፁት።
ባለሥልጣኑ ማድረግ የሚጠበቅበት መገናኛ ብዙሃን ብሔራዊ ደህንነትን አደጋ ላይ በማይጥል መልኩ እና በሙያተኞች መሰራቱን ማረጋገጥ ነው ሲሉም አክለዋል።
የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ መሀመድ ኢድሪስ፤ ደግሞ ባለሥልጣኑ መገናኛ ብዙሃንን በማሸማቀቅ ለውጥ ይመጣል ብሎ እንደማያምን ገልጸው፤ ክትትልና ድጋፍ የማድረግ ሥራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አውስተዋል።
አንጋፋ ጋዜጠኞቹ ያነሱትን ሐሳብ ባለሥልጣኑ በአጭር፣ መካከለኛና በረጅም ጊዜ ወስዶ እንደሚሰራባቸው እና ውይይቱ ጠቃሚ በመሆኑ በቀጣይ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ነው ያነሱት።