ቀጥታ፡

ኢትዮጵያዊነትን ያስቀደመ ምርጫ

ገዛኸኝ ደገፉ/ኢዜአ/

ሀገራት እንደ መልክአምድራዊ ስፋታቸው፣ እንደህዝብ ቁጥራቸው እንዲሁም እንደሚከተሉት የፖለቲካና የአኗኗር ዘይቤ ይመቸናል የሚሏቸውን የመንግስት አስተዳደር ስርአት ይመሰርታሉ። የፖለቲካው ዘርፍ ተንታኞች የመንግስት አስተዳደር ዴሞክራሲያዊ፣ አምባገነናዊ፣ ንጉሳዊ፣ ወታደራዊ የሚሉ ስያሜዎችን በመስጠት ይገልጹታል።

በዴሞክራሲያዊ አስተዳደር ሥርዓት ዜጎች የሚያስተዳድራቸውን አካል ወደ ስልጣን የሚያመጡት በምርጫ ነው። ምርጫ ዜጎች ዴሞክራሲያዊ አስተዳደር የሚለማመዱበት፡ በህዝብ የተወከለ መንግሥት የሚመሰረትበት፡ ለህዝብ የሚጠቅሙ ፓሊሲዎች የሚዘጋጁበት፡ ዜጎች የሀገር ፍቅርን ከዘመናዊ የአኗኗር ዘይቤ ጋር የሚቀስሙበት ስርአት  ስለመሆኑ የተለያዩ ሰነዶች ያመለክታሉ።

ዴሞክራሲያዊ ምርጫን በሚመለከት የተዘጋጁ ሰነዶች እንደሚያመለክቱት ምርጫ በህገመንግስታዊ መርሃ ግብር መሰረት የሚደረግ፣ ብርቱ ፉክክር የተሞላበት፣ ነጻ፡ ተአማኒ፡ አሳታፊ መሆን አለበት። ከዚህ በተቃራኒ ዜጎችን በነጻነት ሳያሳትፉ የሚካሄዱ ምርጫዎች ቅራኔዎችን በመፍጠር አለመግባባቶች እንዲሰፉና ወደ ደም አፋሳሽ ግጭቶች እንዲያመሩ ሲያደርጉ ይታያል።

ለአብነት ለመጥቀስ ያህል በኮንጎ ዴሞክራቲክ፣ በኮትዴቫር፣ በኔፓል፣ በቺሊና በሃይቲ ምርጫን ተከትለው በተፈጠሩ ብጥብጦች ምክንያት በርካቶች ህይወታቸውን አጥተዋል። ራሷን የዴሞክራሲ ቁንጮ አድርጋ በምትወስደው አሜሪካ እንኳ በፈረንጆቹ 2020 መገባደጃ ያካሄደችው ፕሬዝዳንታዊ ምርጫን ተከትሎ በተፈጠረ ነውጥ ቀላል የማይባል ጉዳት ማስከተሉ የሚታወስ ነው።

በኢትዮጵያ ባለፈው ሰኔ 14 ቀን 2013 ዓ.ም የተካሄደው 6ኛው ሀገር አቀፍ ምርጫ ቀደም ሲል በሀገሪቱ ከተካሄዱ ምርጫዎች ልዩ ገጽታ እንደነበረው ብዙዎች የመሰከሩለት እውነታ ነው። ለዚህም አንዱ ማሳያ የሚሆነው በሀገሪቱ በተለያዩ አካባቢዎች በተፈጠሩ የጸጥታ ችግሮች እንዲሁም ከህዳሴው ግድብ ጋር በተያያዘ ከገጠማት ውስጣዊና ውጫዊ ተግዳሮቶች አኳያ ምርጫው በታቀደለት መርሃ ግብር ሰላማዊ ሆኖ ይጠናቀቃል የሚል ግምት በብዙዎች ዘንድ አልነበረም። ስለሆነም ኢትዮጵያውያን በነፃነት ወጥተው ድምጻቸውን እንደሚሰጡ ለመታዘብ ብዙዎች ከቅርብም ከሩቅም ይጠባበቁ ነበር። ነገር ግን በተቃራኒው ምርጫ በተካሄደባቸው የሀገሪቱ ክፍሎች ኢትዮጵያውያን ከሌሊት እስከምሽት ድረስ ዝናብና ጸሐይ ሳይበግራቸው ይመራናል የሚሉትን ለመምረጥ ድምጽ የሰጡበት ሂደት በዓለም አቀፍ ደረጃ ጭምር አድናቆት የተሰጠው ነበር።  

የኢፌዴሪ ህገ መንግስት ስራ ላይ ከዋለበት 1987 ዓ.ም ጀምሮ በሀገራችን የአሁኑን ሳይጨምር ለአምስት ጊዜያት ያህል ሀገር አቀፍ ምርጫዎች ተካሂደዋል፤ ነገር ግን በበርካታ የምርጫ መመዘኛዎች አብዛኞቹ ምርጫዎች ነፃ፣ ፍትሐዊና ተአማኒነት ያላቸው እንዳልነበሩ ብዙዎች የሚመሰክሩት እውነታ ነው። በግንቦት ወር 1997 ዓ.ም የተደረገው ብሄራዊ ምርጫ በተነፃፃሪ የፖለቲካ ምኅዳሩ የሰፋበት፣ ጠንካራ ፉክክር የተስተዋለበት፣ የፖለቲካና የሙያ ማህበራት ተሳትፎ ከፍ ብሎ የታየበት እንደነበር የሚጠቀስ ቢሆንም የምርጫ ውጤት ይፋ ከሆነበት ቀን ማግስት ጀምሮ ሁኔታው ሙሉ በሙሉ የተቀየረበት ነበር።

የምርጫ ውጤት ይፋ መሆንን ተከትሎ በተፈጠሩ ብጥብጦች የጸጥታ ሃይሉ በወሰደው እርምጃ በርካቶች ህይወታቸውን አጥተዋል፤ ሌሎቹ ለአካል ጉዳትና ለእስር ብሎም ደብዛቸው እንዲጠፋ ተደርጓል። በዚህ ምክንያት ብዙዎች “ኢትዮጵያ ውስጥ በምርጫ ለውጥ ማምጣት አይቻልም” ብለው እንዲያስቡና ነፍጥ አንግበው እንዲታገሉ እንዳስገደዳቸው ይናገራሉ። 

በርካታ አፋኝ ህጎች በማውጣት በስልጣን ላይ የመቆየት እድል የነበረው ገዥው ፓርቲ ኢህአዴግ በ2007 ዓ.ም በተካሄደው ምርጫ የፌዴራልና የክልል ምክር ቤቶችን መቀመጫዎች ሙሉ በሙሉ ሊቆጣጠር ችሎ ነበር። ይሁን እንጂ በወጡ አፋኝ ህጎች ነፃነት የራቀው ህዝብ ቁጣው እየገነፈለ መጥቶ በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች ባሰማው ጠንካራ ተቃውሞ የካቲት 2010 ዓ.ም የአመራር ለውጥ እንዲመጣ አስገድዷል።

አዲሱ አመራር ወደ ስልጣን መምጣቱን ተከትሎ ከተወሰዱ የሪፎርም እርምጃዎች መካከል አንዱ የምርጫ ቦርድን በአዲስ መልክ ማደራጀት ነበር። በመሆኑም የብሄራዊ ምርጫ ቦርድን አደረጃጀት፣ አሰራርና የሰው ሀይል በአዲስ መልክ በማደራጀት ገለልተኝነቱን ማረጋገጥ የሚችልበት ቁመና እንዲኖረው መደረጉ በጉልህ ይጠቀሳል፡፡    

ሰኔ 14 ቀን 2013 ዓ.ም የተካሄደው ብሄራዊ ምርጫ እየተቃረበ ሲመጣ ጥቂት የማይባሉ አካላት በተለይም ራሳቸውን የሰብአዊና የፖለቲካ መብቶች ተቆርቋሪና ጠበቃ ያደረጉ አካላት በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች የሰነበቱና ምርጫውን ተመርኩዘው ሊፈጠሩ የሚችሉ አዳዲስ ግጭቶች ይከሰታሉ በማለት ፍላጎትና ስጋታቸውን በአንድም በሌላም መንገድ ሲገልጹ እንደነበር ይታወሳል። ኢንተርናሽናል ክራይስስ ግሩፕ የተሰኘው ዓለም አቀፍ አጥኚ ተቋም ምርጫው በሀገሪቱ ውስጥ የሚታየውን ክፍፍል ሊያሰፋና ሁከትም ሊያቀጣጥል እንደሚችል ተንብዮ ነበር።

በሀገር ውስጥ ይንቀሳቀሱ የነበሩ አንዳንድ የፖለቲካ ድርጅቶችና አክቲቪስቶችም “ኢትዮጵያ አሁን ባለችበት ነባራዊ ሁኔታ ምርጫ ማድረግ ስለማትችል ጊዜያዊ የሽግግር መንግስት እንዲመሰረት” የሚል አቋም ያንጸባረቁበት ሁኔታ ነበር።  ምርጫው በኮቪድ ምክንያት እንዲራዘም የህገ መንግስት ትርጉም መሰረት ተደርጎ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሲወሰን “ለህገ መንግስታዊ ቀውሱ ፖለቲካዊ እንጂ ህጋዊ መፍትሔ የለም” የሚል አቋም የያዙም ነበሩ። ብቸኛው መፍትሔ ብሔራዊ የምክክር መድረክ እንዲፈጠርና ስልጣን የሚያከፋፍል የሽግግር መንግስት እንዲመሰረት ጥሪ ያደረጉም ነበሩ።

ይህ “ሁሉን አቀፍ ውይይት እና የሽግግር መንግስት” አጀንዳ በተለይ በምእራባውያን ዘንድ በግልጽ የተነገረ አቋም ነው። የአሜሪካና የአውሮፓ ህብረት አንዳንድ ባለስልጣናት ኢትዮጵያ ምርጫውን በማራዘም የሽግግር መንግስት እንዲመሰረት ማድረግ አለባት በማለት ህወሃትን ዳግም ወደ ስልጣን ለማምጣት ያለመ አቋም ሲያንጸባርቁ ቆይተዋል።

በግንቦት ወር መጀመሪያ ሳምንት አምስት የአሜሪካ ሴናተሮች “አገራዊ ምርጫው አሁን ባለበት ሁኔታ ነጻ፣ ሚዛናዊ እና ግልጽ ሆኖ ዓለም አቀፍ መመዘኛዎች አያሟላም” ብለው እንደነበር ይታወሳል። በተመሳሳይ የአውሮፓ ህብረት "ምርጫውን ለማካሄድ የሚያስችሉ ሁኔታዎች አልተሟሉም"  በሚል የምርጫ ታዛቢ ቡድን እንደማይልክ በዚያው ሰሞን በሰጠው መግለጫ አሳውቆ ነበር።

በዚህ ምክንያት ብዙዎች የዓለም አቀፍ ተቋማት የዘንድሮው ምርጫ ህዝቡ በነቂስ ወጥቶ ድምጹን ይሰጣል የሚል ግምት አልነበራቸው። ይልቁንም በእለቱ ምርጫውን የሚያደናቅፉ እንቅስቃሴዎች እዚህም እዚያም ይከሰታል የሚል ስጋት ስለነበራቸው ሁኔታውን በጉጉት ይጠባበቁ ነበር። ለዚህም በርካታ ቁጥር ያላቸው ዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃን በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች ተሰማርተው ሂደቱን በንቃት ሲከታተሉ ቆይተዋል።

ይሁን እንጂ ከዚህ በፊት ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ ህዝቡ ሰላማዊ በሆነ መልኩ ድምጹን በመስጠት የሀገሩን ክብር ለዓለም አሳይቷል። ሰኔ 14 ቀን 2013 ዓ.ም ምርጫ አይካሄድባቸውም ተብሎ ከቀሩት ቦታዎች ውጪ በሁሉም የሃገሪቱ ክፍሎች በሚገኙ የምርጫ ጣቢያዎች ከጠዋቱ 12፡00 ሰዓት ጀምሮ ለመራጮች ክፍት ተደርገው የዋሉ ሲሆን መራጩ ህዝብ በብዙ ቦታዎች እስከ ምሽቱ ሶስት ሰአት እንዲቀጥል ተደርጎ ህዝቡ ዲሞክራሲያዊ መብቱን መጠቀሙን መመልከት ተችሏል ፡፡

ከውስጥና ከውጭ በበረታባት ጫና ምክንያት ኢትዮጵያ ምርጫውን ከማድረግ ይልቅ ታራዝመዋለች በማለት ሲጠባበቁ የቆዩት ምእራባውያን ምርጫው ሊካሄድ ቀናት ሲቀሩ ሃሳባቸውን ለማስተካካል ተገደዋል። ቀደም ሲል ቅድመ ሁኔታዎች አልተሟሉም በማለት ምርጫውን እንደማይታዘብ አቋም ይዞ የነበረው የአውሮፓ ህብረት ለምርጫው ታዛቢ መላክ አለመቻሉ ስህተት እንደነበር በማመን መጸጸቱን ገልጿል።

ምርጫው ከተጠናቀቀ በኋላ ባወጣው መግለጫ ኢትዮጵያ ወደ ተሻለ ዴሞክራሲያዊ አስተዳደር መሸጋገሯን እንደግፋለን ከማለቱም በተጨማሪ በምርጫ ህጉ ላይ የተወሰዱ አስፈላጊ ማሻሻያዎች እና በምርጫ ሂደት ውስጥ የነበረው ተሳትፎ እንዲሁም ከፖለቲካ ፓርቲዎች፣ ከሲቪል ማህበራት እና ከመገናኛ ብዙሃን ጋር ለመወያየት በምርጫ ቦርድ የተወሰዱ አዎንታዊ እርምጃዎች እንደነበሩ አስታውሷል፡፡ በምርጫው ቀን ብዙ ሰዎች ሌሊቱን ሙሉ ፈታኝ ሁኔታዎችን ተቋቁመው የሰሯቸውን ተግባራት አድንቋል። የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤትም በተመሳሳይ የምርጫውን ሂደት በበጎ እንደሚመለከተው ገልጿል። መቀመጫቸውን አዲስ አበባ ያደረጉ የካናዳ፤ ጀርመን፤ ጃፓን ኖርዌይ፤ አውስትራሊያ፤ ዴንማርክ፤ ኔዘርላንድ ፤ኒውዝላንድ እና አየርላንድ ኤምባሲዎች በእንግሊዝ ኢምባሲ በኩል ባወጡት መግለጫ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ለምርጫው ስኬት ያደረገውን ጥረት አድነቀዋል። እነዚህ ተቋማት ቀደም ሲል ጠብቀውት ከነበረው ሁኔታ አኳያ ምርጫው በተቃራኒው ሰላማዊ መሆኑን ሲመለከቱ “ምርጫ ብቻውን የዴሞክራሲ ሪፎርም ማረጋገጫ አይደለም” ወደ ማለት አዘንብለዋል።

ምእራባውያን መንግስታት በተለይም የአሜሪካ መንግስት ባለስልጣናት በሰብአዊ መብቶች መከበርና በዴሞክራሲያዊ ስርአት መስፈን ሽፋን በኢትዮጵያ የህዝብ ተወካዮች ምክርቤት በሽብርተኝነት የተፈረጁት ህወሃትና ኦነግ የተካተቱበት ሁሉን አቀፍ የሽግግር መንግስት እንዲመሰረት በማድረግ በኢትዮጵያ በፖለቲካ ፓርቲዎችና በግለሰቦች ውዝግብ ጊዜውን የሚያባክን እጅግ ደካማና ልፍስፍስ መንግስት እንዲፈጠር ፍላጎታቸው መሆኑን ከሰጧቸው አስተያየቶች መረዳት አያዳግትም። 

የአፍሪካ ህብረት የምርጫ ታዛቢ ቡድንን በመምራት ሰኔ 14 ቀን 2013 ዓ.ም.የተካሄደዉን ምርጫ የታዘቡት የቀድሞዉ የናይጀሪያ ፕሬዝዳንት ኦልሴጉን ኦባሳንጆ በአጠቃላይ ከሂደቱ ጀምሮ አሳታፊ እና ዴሞክራሲያዊ አካሂድን የተከተለ መሆኑን በምርጫዉ ዕለትም ካጋጠመው መለስተኛ የምርጫ የቁሳቁሶች እጥረት ባሻገር አሳታፊ፤ ነፃ እና ገለልተኛ እንደነበር የገለጹ ሲሆን የምስራቅ አፍሪካ ተጠባባቂ ኃይል የምርጫ ታዛቢ ቡድን በበኩሉ “ጠቅላላ ምርጫው በአብዛኛው የአገሪቷ አካባቢዎች የተረጋጋና ሰላማዊ ድባብ ተላብሶ መካሄዱን ታዝቤያለሁ" ሲል ተናግሯል።

የዘንድሮው ምርጫ የድምፅ አሰጣጥ ሂደት ከሰብዓዊ መብቶች አጠባበቅ አንጻር በብዙ መልኩ የተሳካ እንደነበር የገለጹት የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን ኮሚሽነር ዶክተር ዳንኤል በቀለ፤ የምርጫው ዕለት የጎላ ችግር ሳይከሰት በሰላም ተጀምሮ የተጠናቀቀበትና በሰብአዊ መብቶች አጠባበቅ ረገድ በብዙ መልኩ የተሳካ የድምፅ አሰጣጥ ሂደት እንደነበር አብራርተዋል። በሌላ በኩል ምርጫው በተደረገባቸው የሃገሪቱ ክፍሎች ከ2ሺ በላይ ታዛቢዎችን አሰማርቶ እንደነበር የገለጸው የኢትዮጵያ ሲቪል ማህበራት ህብረት ይፋ ባደረገው የመጀመሪያ ደረጃ ሪፖርቱ ህዝቡ ለመምረጥ ያሳየው ፍላጎት፣ እንዲሁም የሴቶች ተሳትፎ መጉላት ጣቢያዎች በተነጻጻሪ ለአቅመ ደካሞችና አካል ጉዳተኞች አመቺ ሆነው መዘጋጀታቸው አበረታች ነበር ብሏል።

በኢትዮጵያ የፖለቲካ እንቅስቃሴዎች ውስጥ እንግዳ ያልሆኑ፡ የ2002ቱ ምርጫ ብቸኛ የተቃዋሚ የፓርላማ አባል የነበሩትና ኢዜማን ወክለው የተወዳደሩት አቶ ግርማ ሰይፉ ማሩ የምርጫውን በሰላም መጠናቀቅ ተከትሎ በይፋዊ የትዊተር ገጻቸው ባሰፈሩት አስተያየት ለብሽሽቅ ጊዜ የለንም! ያመንበትን ሰርተናል "ዜጎች ይመርጣሉ፣ ኢትዮጵያ ታሽንፋለች!"ብለን ሠርተናል። ኢትዮጵያ እንድታሽንፍ ሰርተን፤ምርጫው በሠላም ተጠናቋል! ይህ ድል የሠላም ወዳዶች እንጂ የጠብ ጠንሳሾች አይደለም “ በማለት ነበር የገለጹት።

አንጋፋው የምጣኔ ሃብት ምሁር ብርሃነ መዋም ኢትዮጵያ ላደረገችው ምርጫ ፍትሃዊነት ከአሜሪካ ወይም ከአውሮፓ ህብረት ምንም አይነት ማረጋገጫ ማግኘት አያስፈልጋትም፡፡ ውስጣዊ የሆኑ አንዳንድ ጉዳዮች ቢኖሩም ምርጫው ነፃ እና ፍትሃዊ በሆነ መልኩ መደረጉ እንደታየ ገልጸው፤ ምርጫው ኢትዮጵያ ነጻና ሉአላዊት የአፍሪካ ሃገር መሆኗዋ ግልጽና ጎላ አድርጎ አሳይቷል ብለዋል። ኢዜአ ያነጋገራቸው ምሁራን በበኩላቸው ምርጫው ሰላማዊና ዲሞክራሲያዊ ሆኖ መጠናቀቁ ኢትዮጵያዊያን በሀገራቸው ጉዳይ እንደማይደራደሩ በተግባር ያሳየ መሆኑን ገልጸዋል። መራጩ ህዝብ ያሳየው ቁርጠኝነት ለሀገሩ ያለውን ፍቅርና ለጠላት የማይንበረከክ መሆኑን ግልፅ መልእክት ያስተላለፈበት እንደነበርም አመልክተዋል።

በዘንድሮው ምርጫ የታየው ሰላማዊነት እና ስልጡን አካሄድ በድህረ ምርጫውም ተጠናክሮ መቀጠል አለበት። በርካታ አስተያየት ሰጪዎች እንደሚናገሩት የምርጫው ውጤት ምንም ይሁን ምን የተገኘውን በጸጋ መቀበል የሀገርና የሕዝብን ጥቅምና ፍላጎት ማክበር ይገባል። በቀጣይም ኢትዮጵያውያን ለሰላምና ለዴሞክራሲ መሰረት በመጣል የጀመሩትን ሂደት ሊያጎለብቱትና ወደ ላቀ ደረጃ ሊያሸጋግሩት ይገባል።  

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም