ኦ ኤም ኤን በኦሮሚያ የተገኘውን ስኬት ወደ ላቀ ደረጃ ለማድረስ ከክልሉ ሕዝብና መንግሥት ጋር እንዲሰራ ተጠየቀ

100
አዲስ አበባ ሀምሌ 29/2010 ኦሮሚያ ሚዲያ ኔትውርክ (ኦኤምኤን) በኦሮሚያ እስካሁን የተገኘውን ስኬት ወደ ላቀ ደረጃ ለማድረስ ከክልሉ ሕዝብና መንግሥት ጋር ሊሰራ እንደሚገባ ፕሬዝዳንት ለማ መገርሳ ተናገሩ። የኦኤምኤን የክልሉ ከፍተኛ ባለሥልናት፣ የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባን ጨምሮ የተለያዩ የመንግስት የስራ የሥራ ኃላፊዎች በተገኙበት ዛሬ ቅርጫፍ ቢሮውን ከፍቷል። የክልሉ ፕሬዝዳንት አቶ ለማ መገርሳ በዚሁ ወቅት እንደገለጹት፤ ኦኤምኤንና ዳይሬክተሩ ጃዋር መሀመድ እስካሁን ኦሮሚያ ውስጥ ለመጣው ለውጥ ትልቁን አስተዋጽኦ በማበርከታቸው ምስጋና ይገባቸዋል። ''ሚዲያው አሁን የተገኘውን ድል የበለጠ ስኬታማ ለማድረግ ሕዝቡን ማነሳሳትና ማጠናከር ይኖርበታል'' ሲሉ ነው ፕሬዝዳንቱ ያስገነዘቡት። ''የጀመርነውን ጉዞ ከዳር ለማድረስ የሁሉም አካላት ድርሻ ያስፈልጋል'' ያሉት አቶ ለማ በተለይ ወጣቱ የሕዝቡ መከታ ሆኖ መቀጠል   እንደሚጠበቅበት አመልክተዋል። ''የተገኘው ለውጥ በከባድ መስዋዕትነት የመጣ በመሆኑ ወጣቶች የተገኘውን ስኬት በመንከባከብ ወደ ተሻለ ደረጃ ማድረስ አለባቸው'' ሲሉ ጥሪ አቅርበዋል። ሁሉም የኦሮሚያ ድርጅቶችና ምሁራን አሁን የመጣው አንድነት አካል በመሆን እንዲሰሩም ጠይቀዋል። ''አሁንም ተበታትናችሁ የምትገኙ ድርጅቶች ወደ አገር ውስጥ በመምጣት የተገኘውን ድል ወደ ፊት እንውሰደው'' ብለዋል። የኦኤምኤን ዳይሬክተር ጃዋር መሀመድ በበኩሉ በክልሉ እስካሁን ለተመዘገበው ውጤት በወጣቱ ስም የክልሉን ፕሬዚዳንት አቶ ለማ መገርሳን ማመስገን እንደሚፈልግ ተናግሯል። በስነስርዓቱ ወቅት በግሉ ይገለገልበት የነበረውን ላፕቶፕ ኮምፒውተር ለአቶ ለማ አበርክቷል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም