ከድህነት ለመውጣትና አገርን ለማበልፀግ ስራ ፈጣሪ እጆች ያስፈልጉናል --ም/ከንቲባ አዳነች አቤቤ - ኢዜአ አማርኛ
ከድህነት ለመውጣትና አገርን ለማበልፀግ ስራ ፈጣሪ እጆች ያስፈልጉናል --ም/ከንቲባ አዳነች አቤቤ
አዲስ አበባ፤ ሰኔ 22 ቀን 2013 (ኢዜአ) ከድህነት ለመውጣትና አገርን ለማበልፀግ ሥራ ፈጣሪ እጆች ያስፈልጉናል ሲሉ የአዲስ አበባ ከተማ ምክትል ከንቲባ አዳነች አቤቤ ተናገሩ።
በጄኔራል ዊንጌት ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ የምስራቅ አፍሪካ ቀጠናዊ የቴክኒክና ሙያ ትምህርት ስልጠና የልህቀት ማዕከል ፕሮጀክት የህንፃ ግንባታ የመሰረት ድንጋይ ተቀምጧል።
የመሰረት ድንጋዩን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ አዳነች አቤቤ እና የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስትር ዶክተር ሳሙኤል ኡርቃቶ አስቀምጠዋል።
በዚህ ወቅት ንግግር ያደረጉት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ አዳነች አቤቤ ከድህነት ለመውጣትና ሀገራችንን ለማበልፀግ ሥራ ፈጣሪ ዜጎችን ማፍራት እንደሚገባ ተናግረዋል።
ከተማ አስተዳደሩ ለሀገር ብልጽግና የሚያስፈልጉ የሰው ኃይል ለሚያፈሩ ተቋማት ቅድሚያ በመስጠት አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግም ቃል ገብተዋል።
የጄኔራል ዊንጌት ቴክኒክና ሙያ ኮሌጅ አንጋፋና የሀገር ባለውለታ ዜጎችን ያፈራ ተቋም መሆኑን አንስተው፤ ከተማ አስተዳደሩ ተቋሙን ወደ ዩኒቨርስቲ ለማሳደግ እንደሚሰራም ተናግረዋል።
የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስትር ዶክተር ሳሙኤል ኡርቃቶ በበኩላቸው ወጣቶች በዕውቀት የዳበሩና ሥራ ፈጣሪ እንዲሆኑ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ከዓለም ባንክ ጋር በመሆን የተለያዩ ፕሮጀክቶችን ቀርፆ እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል።
የሚተገበሩት ፕሮጀክቶች ችግር ፈቺና ከሀገር ውስጥ ባሻገር ለጎረቤት ሀገራት አስተዋጽኦ እንደሚኖራቸው ያላቸውን እምነት ገልፀዋል።
በቀጣይ ተጨማሪ ሁለት ፕሮጀክቶች እንደሚጀመሩም ጠቁመዋል።
የመሰረት ድንጋይ የተቀመጠለት የጄኔራል ዊንጌት ፖሊ ቴክኒክ የምስራቅ አፍሪካ ቀጠናዊ የቴኒክና ሙያ ትምህርትና ሥልጠና የልህቀት ማዕከል ግንባታ በውስጡ የአስተዳደር ህንፃ፣ የመማሪያ ክፍሎች፣ ቤተ-ሙከራ፣ የመኝታ ክፍሎችና የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎችን ያካተተ ነው ።
የፕሮጀክት ወጪው ከዓለም ባንክ በተገኘ 14 ነጥብ 85 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር እንደሚሸፈን ተገልጿል፡፡