የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ሙዚዬም ሊመሰረት ነው - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ሙዚዬም ሊመሰረት ነው
አዲስ አበባ፤ ሰኔ 22 ቀን 2013 (ኢዜአ) በመላው ዓለም የሚገኙ የኢትዮጵያ ቅርሶች በኢትዮጵያ ተሰባስበው የሚቀመጡበት የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ሙዚየም ሊቋቋም መሆኑ ተገለጸ።
አቶ አለባቸው ደሳለኝ በሙያቸው የፎቶግራፍ ጋዜጠኛ ሲሆኑ፤ በእንግሊዝ ሀገር ለንደን ይኖራሉ።
'የኢትዮጵያ ፕሮሞሽን ሄርቴጅ አሶሴሽን' የተባላ የግብረ ሰናይ ድርጅት በማቋቋም ላለፉት 24 ዓመታት በተለያዩ ምክንያቶች ወደ ውጭ ሀገር የወጡ የኢትዮጵያን ቅርሶችን ሲያሰባስቡ ቆይተዋል።
ማህበሩ ቅርሶቹን በግዢና በሌሎች ሕጋዊ መንገዶች የሚያሰባስብ ሲሆን፤ አውድ ርዕዮችን በማዘጋጀት የኢትዮጵያን ታሪክ ባህልና ቅርስ ሲያስተዋውቅ ቆይቷል።
ማህበሩ ያሰባሰባቸውን ቅርሶች ወደ ኢትዮጵያ ይዞ በመምጣትም የዲያስፖራ ሙዚዬም ለማቋቋም ዝግጅ ማጠናቀቁን አቶ አለባቸው ለኢዜአ ተናግረዋል።
በተጨማሪ በዝርፊያ ተመዝብረውና በተለያዩ ምክንያቶች ከሀገር የወጡ ታሪካዊ ቅርሶችን በገንዘብ ገዝቶ በማሰባሰብ በሙዚዬሙ እንዲቀመጡ እንደሚደረግም አንስተዋል።
ዳያስፖራው ማህበረሰብ ከቤተሰቦቻቸው የወረሷቸው ቅርሶች በሙዚዬሙ በትውስት እንዲያስቀምጡ ይደረጋልም ነው ያሉት።
ሙዚዬሙ የሰው ልጆች ያለ ምንም የዘር ልዩነት የኢትዮጵያን ታሪክ እንዲሁም የአፍሪካ ስልጣኔን በተለያዩና ብርቅ በሆኑት ቅርሶቻችን እንዲማሩባቸው የማድረግ ዓላማ እንዳለውም አብራርተዋል።
ወጣቱ ትውልድ የሀገሩን አኩሪ ባህልና ታሪክ እንዲማር ከማድረጉም ባሻገር ለጎብኚዎች የኢትዮጵያን ቀደምት ስልጣኔ በማስተዋወቅ ረገድ ጉልህ ድርሻ እንደሚኖረው ነው የጠቆሙት።
የሙዚዬሙ መቋቋም ለታሪክ ተመራማሪዎችና የዘርፉ ምሁራን አብርክቶው ጉልህ እንደሚሆንም ያላቸውን እምነት ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ ቅርሶች የኢትዮጵያን ስልጣኔ እንደመጽሃፍ ገልጸው ያስነብባሉ ያሉት አቶ አለባቸው፤ የሙዚዬሙ መመስራት ቀደምት አባቶቻችን ለዓለም ታሪክ ያበረከቱት አስተዎጽኦ እንዲታወቅ እድል እንደሚከፍት ተናግረዋል።
በተለያዩ ክፍለ ዓለማት የሚኖረው የዳያስፖራ ማህበረሰብ በሚኖሩበት ሀገር ያሉ የኢትዮጵያ ቅርሶች ወደ ሀገር ቤት እንዲመለሱ የበኩላቸውን አስተዋጽኦ እንዲያደርጉም ጥሪ አቅርበዋል።
በ1868 ዓ.ም በኢትዮጵያና በእንግሊዝ መካከል በተካሄደው የመቅደላ ጦርነት "ለእንግሊዞች እጄን አልሰጠም" በማለት ራሳቸው ያጠፉት የአፄ ቴዎድሮስ ሽሩባ ፀጉር(ቁንዳላ) ከ150 ዓመት የእንግሊዝ ሀገር ቆይታ በኋላ በመጋቢት ወር 2011 ዓ.ም ወደ ኢትዮጵያ መመለሱ ይታወሳል።