ቀጥታ፡

ባንኩ ከ2 ቢሊዮን ዶላር በላይ ገንዘብ በምንዛሬ ወደ ሀገር ውስጥ ማስገባቱን ገለጸ

ሰኔ 22 ቀን 2013 (ኢዜአ) የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በዘንድሮው በጀት ዓመት ከ2 ቢሊዮን ዶላር በላይ ገንዘብ በምንዛሬ ወደ ሀገር ውስጥ ማስገባቱን አስታወቀ።

ባንኩ ይህን ያስታወቀው ለ22ተኛ ግዜ ያዘጋጀው "ይቀበሉ፣ ይመንዝሩ ፣ ይሸለሙ " የውጪ ምንዛሬ ግኝት ማበረታቻ የባለዕድለኞች ዕጣ ቁጥር ይፋ ባደረገበት ወቅት ነው።

ባንኩ ከብሔራዊ ሎተሪ ጋር በመተባባር በተዘጋጀው የዕጣ ማውጣት ሥነሥርዓት ሶስት ባለእድለኛ ዕጣዎች ይፋ ተደርገዋል።

በዚህም በ1ኛ ዕጣ የቤት አውቶሞቢል ፣ በ2ተኛ ዕጣ ሁለት ባለሦስት እግር ተሸከርካሪ እና በሶስተኛ ዕጣ 20 ላፕቶፕ ኮምፒተሮችን የሚያሸልሙ እጣዎች የፋ ተደርገዋል።

የ1ኛ ዕጣ የቤት አውቶሞቢል የባለ ዕድል ቁጥር 8092804 ሆኖ የወጣ ሲሆን፤ በ2ተኛ ዕጣ የመጀመሪያ ባለሦስት እግር ተሸከርካሪ እጣ ቁጥር 8088295 ሆኗል።

ሁለተኛ የባለሦስት እግር ተሸከርካሪ የባለዕድል ቁጥር ደግሞ 8013712 በመሆን ይፋ ተደርጓል።

በሦስተኛ ዕጣ 20 ላፕቶፕ ኮምፒተሮች እያንዳንዳቸው በወጣላቸው ዕጣ መሰረት ለባለዕድለኞች ወተዋል።

በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ኤክስፐርትና ኢንካሚንግ ዳይሬክተር የሆኑት አቶ ጌጡ ብሩ የሽልማት መርሃ- ግብሩ ዜጎች ከውጪየሚላክላቸውን ገንዘብ በባንክ ብቻ እንዲመነዝሩ እንደሚያበረታታ ተናግረዋል።

ወደ ሀገር ውስጥ ከሚገባው የውጪ ሀገር ገንዘብ አብዛኛው የሚሰበሰበው በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በኩል መሆኑን ጠቅሰው፤ በ2013 የበጀት ዓመት በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በኩል 2.4 ቢሊዮን ዶላር የሚጠጋ ገንዘብ  ወደ ሀገር ውስጥ መግበቱን ገልፀዋል።

ባንኩ ኅብረተሰቡንም በማስተማር እና የተለያዩ የሽልማት መርሃ- ግብሮችን በማስተዋወቅ ከውጭ የሚላክ ገንዘብ ባንክ በኩል እንዲያልፍ ከፍተኛ ጥረት እያደረገ መሆኑን ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በ21ኛው ዙር "ይቀበሉ፣ ይመንዝሩ ፣ ይሸለሙ"ለመርሐ ግብሮች ከ46.2 ሚሊን ብር በላይ ግምት ያላቸው ሽልማቶችን ለደንበኞች መሸለሙን ከባንኩ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም