ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ከዳር እንዲደርስ ድጋፋቸውን እንደሚቀጥሉ የጎንደር ከተማ ነዋሪዎች ተናገሩ - ኢዜአ አማርኛ
ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ከዳር እንዲደርስ ድጋፋቸውን እንደሚቀጥሉ የጎንደር ከተማ ነዋሪዎች ተናገሩ
ጎንደር ሀምሌ 29/2010 ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የኢንጂነር ስመኘው በቀለ መታሰቢያ ሆኖ ግንባታው ከዳር እንዲደርስ ድጋፋቸውን እንደሚቀጥሉ የጎንደር ከተማ ነዋሪዎች ተናገሩ፡፡ የከተማውና አካባቢው ነዋሪዎች የኢንጂነር ስመኘው በቀለ ወላጅ አባት በተገኙበት በከተማው የአጼ ፋሲል ስቴዲየም ዛሬ የመታሰቢያ የሀዘን ስነ-ስርዓት አካሂደዋል፡፡ " ኢንጂነር ስመኘው ህይወቱን የሰጠለት የህዳሴ ግድብ ከፍጻሜ እንዲደርስ በገንዘብ፣ በጉልበትና በሀሳብ ከመደገፍ ወደኋላ አንልም "ያለው በሀዘን ስነ-ስርቱ ላይ የተገኘው ወጣት አለምሸት አስፋው ነው፡፡ የኢንጂነር ስመኘውን ፈለግ በመከተል ታሪክ ለመስራት ቆርጠው መነሳታቸውን የተናገረው ወጣት አለምሸት "የኢንጂነሩ ገዳዮች ተጣርተው ለፍርድ መቅረብ አለባቸው"ብሏል፡፡ ከጎንደር ዙሪያ የመጡት አቶ አለቃው ጥጋቡ በበኩላቸው " በኢንጂነሩ ሞት ሀዘናችን የበረታ ቢሆንም ባከናወነው አኩሪ ተግባር ሁሌም በታሪክ ሲዘከር የሚኖር ታላቅ የልማት አርበኛ ነው" ብለዋል፡፡ ጀግና ቢሞት ጀግና ይተካል በልማት አርበኛው ኢንጂነር ስመኘው ሲመሩት የነበረውን የህዳሴ ግድብ ከፍጻሜ ለማድረስ ኢትዮጵያዊያን ዛሬም እንደትናንቱ በቁጭት መንፈስ ድጋፋቸውን በመቀጠል ግድቡን ከማጠናቀቅ ወደ ኋላ እንደማይሉ እምነታቸው መሆኑንም አመልክተዋል፡፡ የከተማው የሀገር ሽማግሌዎች ተወካይ አቶ ባዩ በዛብህ በቀን የሀሩር ፀሐይ በሌሊትና በክረምት ጭምር ደፋ ቀና ሲሉ ህይወታቸው ባለፈው ኢንጂነር ስመኘው በቀለ ሞት የጎንደር ህዝብ መራር ሀዘን እንደተሰማው ገልጸዋል፡፡ " ለሀገራችን ልማትና እድገት ሲታትር የነበረው ኢንጂነር ስመኘው ቢሞትም ተግባሩ ህያው ሆኖ ይኖራል" ያሉት አቶ ባዩ የታላቁን የህዳሴ ግድብ ግንባታ የሚያቆመው አንዳችም ኃይል እንደናይኖር ተናግረዋል፡፡ በሀዘን ስነ-ስርዓቱ ወቅት የጎንደር ከተማ ከንቲባ አቶ ተቀባ ተባባል ባደረጉት ንግግር "ኢንጂነር ስመኘው በቀለ ጎንደር ወልዳ አሳድጋ ለቁም ነገር አብቅታ ለሀገራችን መርጣ ከሰጠቻቸው ጥቂት ብርቅዬ ምሁራን አንዱ ናቸው" ብለዋል፡፡ ኢንጂነር ስመኘው የተሰጣቸውን ሀገራዊ ኃላፊነት በአይበገሬነት፣ በፍጹም መልካም ስነ-ምግባርና ተግባቢነት በውጤታማነት ሲወጡ የቆዩ ከሀገሪቱ የቁርጥ ቀን ልጆች ግንባር ቀደም እንደነበሩም አመልክተዋል፡፡ "ከተማ አስተዳደሩ ለወላጅ አባቱና ቤተሰቦቻቸው አስፈላጊውን ድጋፍ ለማድረግ ተዘጋጅቷል” ያሉት ከንቲባው የኢንጂነሩ ገዳዮች ተጣርተው ለፍርድ እንዲቀርቡም አሳስበዋል፡፡ " በልጄ ሞት ሀዘኔ የከፋ ቢሆንም የኢትዮጵያ ህዝብ ከዳር እስከ ዳር ልቡ በሀዘን ተነክቶ የጀግና ቀብር ስነ-ስርዓት በማድረጉ ምስጋናዬ ወደር የለውምና አምላክ ኢትዮጵያን ይባርክ" ያሉት የኢንጂነር ስመኘው ወላጅ አባት አቶ በቀለ አይናለም ናቸው፡፡ ከከተማው የተለያዩ አድባራት የተውጣጡ የኃይማኖት አባቶች ስርዓተ ፍታትና ጸሎት ያካሄዱ ሲሆን ህዝቡና አመራሩም የኢንጂነሩን ቤተሰቦች ከአጼ ቴዎድሮስ አውሮፕላን ማረፊያ ጀምሮ በደማቅ ስነ-ስርዓት አቀባበል አድርጎላቸዋል፡፡