የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ለኢትዮጵያ ኦሎምፒክ ኮሚቴ የ15 ሚሊዮን ብር ድጋፍ አደረገ - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ለኢትዮጵያ ኦሎምፒክ ኮሚቴ የ15 ሚሊዮን ብር ድጋፍ አደረገ
አዲስ አበባ፣ ሰኔ 21 ቀን 2013 (ኢዜአ) የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ዘንድሮ በሚካሄደውን የቶኪዮ ኦሎምፒክ ዝግጅት ለሚሳተፈው የኢትዮጵያ ልዑክ ያለውን አጋርነት ለመግለጽ ለኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ የ15 ሚሊዮን ብር ድጋፍ አደረገ።
ባንኩ የገንዘብ ድጋፉን አስመልክቶ በሰጠው መግለጫ የባንኩ ፕሬዝዳንትና ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቤ ሳኖ ድጋፉ የኦሎምፒክ ተሳታፊ ስፖርተኞችን ለማበረታታት፣ የደርሶ መልስ ወጪያቸውን ለመሸፈንና ለአቀባበል ሥነ-ሥርዓት እንደሚውል ገልጸዋል።
ለኦሎምፒክ ዝግጅት በሞባይል ባንክና ሲቢኢ ብር በኩል ህብረተሰቡ ድጋፍ ማድረግ የሚችልበትን ሁኔታ ባንኩ ማመቻቸቱንም ተናግረዋል።
በዚህም ሁሉም የኢትዮጵያዊ የኦሎምፒክ ቡድኑን በመደገፍ የበኩሉን አስተዋጽኦ እንዲያደርግ ጥሪ አቅርበዋል።
የኢትዮጵያ ኦሎምፒክ ኮሚቴ ፕሬዚዳንት ዶክተር አሸብር ወልደጊዮርጊስ በበኩላቸው የኦሎምፒክ ቡድኑ ለስምንት ወራት ልምምድ ማድረጉን ተናግረዋል።
አብዛኛውን ጊዜ የገንዘብ ድጋፍ የሚደረገው ከውድድሮች መልስ መሆኑን አስታውሰው፤ "ድጋፉ ከኦሎምፒክ ተሳትፎ በፊት መደረጉ ከሌላው ጊዜ ልዩ ያደርገዋል" ብለዋል።
የገንዘብ ድጋፉ የኦሎምፒክ ቡድኑ ስራ በማገዝ ረገድ ሚናው የጎላ መሆኑንም አንስተዋል።
ባንኩ የገንዘብ ድጋፍ ከማድረግ ባሻገር ኅብረተሰቡ ተሳታፊ የሚሆንበትን አሠራር ማዘጋጀቱን አድንቀው፤ ሌሎችም ባንኮችና ኢንተርፕራይዞች እንዲህ አይነቱን በጎ ዓላማ እንዲከተሉ ጥሪ አቅርበዋል። በጃፓን ቶኪዮ በሚካሄደው 32ኛው የኦሎምፒክ ውድድር ላይ በአትሌቲክስ ዘርፍ ከሚጠበቁ አገሮች መካከል ኢትዮጵያ አንዷ ናት።