ቀጥታ፡

ፖለቲካ ፓርቲዎች በድህረ-ምርጫ የሚያደርጉት እንቅስቃሴ የህዝብን አንድነት የሚያጠናክር እንዲሆን ተጠየቀ

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 21 ቀን 2013 (ኢዜአ) በስድስተኛው ጠቅላላ ምርጫ የተወዳደሩ ፖለቲካ ፓርቲዎች በድህረ-ምርጫ ወቅት የሚያደርጉት እንቅስቃሴ የህዝብን አንድነት የሚያጠናክር እንዲሆን ተጠየቀ።

የምሥራቅ አፍሪካ ፖሊሲ ጥናት ተቋም ምክትል ዳይሬክተር ዶክተር ብርሃኑ ሌንጂሶ እና የሰብዓዊ መብት ተሟጋቹ ኦባንግ ሜቶ በምርጫና ተያያዥ ጉዳዮች ላይ ከኢዜአ ጋር ቆይታ አድርገዋል።

የሰብዓዊ መብት ተሟጋቹ  ኦባንግ ሜቶ የቅድመ-ምርጫና የምርጫ ወቅት ሰላማዊ እንዲሆን የፖለቲካ ፓርቲዎች ሚና ከፍተኛ እንደነበር አውስተዋል።

ፓርቲዎች አገር ከፖለቲካ በላይ በመሆኗ አገርና ህዝብን በማስቀደም የህዝብን ድምጽ አክብረው መንቀሳቀስ እንደሚገባቸው መክረዋል።

እንደ ሰብዓዊ መብት ተሟጋቹ ገለጻ፤ ፖለቲካን የሰውን ህይወት ለመቀየር በመጠቀም በሰለጠነ መንገድ የህዝብን ድምጽ አክብሮ መንቀሳቀስ ይገባል።

ቀደም ሲል ከነበሩ የድህረ-ምርጫ ሁነቶች በመማር አገርና ህዝብን አደጋ ላይ ሊጥሉ ከሚችሉ እንቅስቃሴዎች መቆጠብ እንደሚገባም ገልጸዋል።

በቅድመ-ምርጫና በምርጫ ወቅት የተስተዋለውን ሰላም ለማስቀጠል ፖለቲካ ፓርቲዎች አጠቃላይ ውጤቱ ይፋ በሚሆንበት ወቅትም ደጋፊዎቻቸውና አባሎቻቸውን ኃላፊነት በተሞላ መንገድ እንዲንቀሳቀሱ ማድረግ እንዳለባቸው አስገንዝበዋል።

በተጨማሪም ከሚናገሩት ቃላት ጀምሮ የህዝብን አንድነት የሚያጠናክሩና የአገርን ሰላም የሚያስቀጥሉ መሆን እንዳለባቸው መክረዋል።

የምሥራቅ አፍሪካ ፖሊሲ ጥናት ተቋም ምክትል ዳይሬክተር ዶክተር ብርሃኑ ሌንጂሶ በበኩላቸው በምርጫው የተወዳደሩ ፖለቲካ ፓርቲዎች እስካሁን ያሳዩት ስነ-ምግባር ከሞላ ጎደል የተሻለ እንደሆነ ተናግረዋል።

ይህም የኢትዮጵያ ፖለቲካ ባለፉት ሦስት ዓመታት መሻሻል ማሳየቱን የሚያመላክት መሆኑን አመልክተዋል።

"በምርጫው እለት ህዝብ ድምጽ ለመስጠት ላሳየው ትዕግስት ክብር በመስጠት በድህረ- ምርጫ የሚደረጉ እንቅስቃሴዎች በጥንቃቄ መሆን ይጠበቅባቸዋል" ሲሉ አክለዋል።

የዴሞክራሲን መንገድ ለማስቀጠል የህዝብ ውሳኔ ማክበር የመጀመሪያው መሆኑን አስታውሰው፤ ውጤቱ ይፋ ሲሆን የህዝብን ድምጽ ማክበር ወሳኝ መሆኑን አንስተዋል።

በኢትዮጵያ ባለፉት 30 ዓመታት ህዝብ ምርጫ ቢያደርግም ድምጹን በትክክል ማግኘት አለመቻሉን አውስተው፤ በስድስተኛው ጠቅላላ ምርጫ የታየውን አዲስ ታሪክ ለማስቀጠል በኃላፊነት መሥራት እንደሚጠይቅ ነው ያብራሩት።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም