ቀጥታ፡

40 በመቶ የሚሆነውን ሀገራዊ የዘይት ፍላጎት በሀገር ውስጥ ምርት መሸፈን መቻሉን የንግድ ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር

ሰኔ 21/2013 (ኢዜአ) 40 በመቶ የሚሆነውን ሀገራዊ የዘይት ፍላጎት በሀገር ውስጥ ምርት መሸፈን መቻሉን የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር አስታወቀ።

የግብዓት እጥረትና የግብይት ሰንሰለት ውስብስብነት በምግብ ዘይት አቅርቦት ላይ ተጽእኖ እየፈጠረ መሆኑንም ሚኒስቴሩ ይፋ አድርጓል።

ሚኒስቴሩ በዘይት አቅርቦትና ግብይት ላይ ያከናወነውን ጥናት አስመልክቶ ዛሬ ውይይት ተደርጓል።

በውይይቱም የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስትር መላኩ አለበለና የግብርና ሚኒስትር ዑመር ሁሴን ጨምሮ የዘይት አምራቾችና ሌሎች ባለደርሻ አካላት ተሳትፈዋል።

የምግብ ፣ መጠጥና ፋርማሲዩቲካል ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት ምክትል ዋና ዳይሬክተር በቀለ መኩሪያ ጥናቱን ባቀረቡበት ወቅት የኢትዮጵያ ዓመታዊ የምግብ ዘይት ፍላጎት 907 ሚሊዮን ሊትር እንደሚደርስ ገልጸዋል።

ይህን ፍላጎቱን ለመሸፈን በዓመት 840 ሚሊዮን ሊትር ዘይት ከድፍድፍ ፓልም  እንደሚመረት አክለዋል።

በፍላጎትና በአቅርቦት መካከል ያለውን የ7 ነጥብ 4 በመቶ ልዩነት በአገር ዉስጥ ባሉ አነስተኛና መካከለኛ የዘይት አምራቾችና በነጻ ገበያ ከውጪ በሚገባ ዘይት የሚሸፈን ይሆናል ብለዋል።

የምግብ ዘይት ፍላጎቱን ለመሸፈን ለድፍድፍ ፓልም ዘይት ግዥ በዓመት 993 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር እንደሚያስፈልግም ነው የተናገሩት።

በአሁኑ ወቅት በማምረት ሂደት ላይ የሚገኙና ማጣሪያ ያላቸው የዘይት ፋብሪካዎች ብዛት 30 መድረሱን ጠቅሰው፤ በዚህም 40 በመቶ የሚሆነውን ሀገራዊ የዘይት ፍላጎት በሀገር ውስጥ ምርት መሸፈን መቻሉን ተናግረዋል።

የቅባት እህሎች አመራረት ዘመናዊ አለመሆን፤የግብይት ሰንሰለቱ ውስብስብነትና የግብይት ውል ስርዓት አለመኖር በምግብ ዘይት አቅርቦት ላይ ተጽእኖ እየፈጠረ መሆኑንም ጨምረው ገልጸዋል።

የቅባት እህል አምራቾችን በቴክኖሎጂ በመደገፍና በሽታን የሚቋቋሙ ዝርያዎችን በማቅረብ ምርቱን ማሳደግ እንደሚገባም ተናግረዋል።

ለዘይት አምራች ኢንዱስትሪዎች የመሬት አቅርቦት ድጋፍ በማድረግ በግብዓት አቅርቦቱ ላይ ተሳታፊ አንዲሆኑ ማስቻልም ሌላኛው አማራጭ መሆኑን ጥናት አቅራቢው አንስተዋል።

የምግብ ዘይት የኮንትሮባንድ ንግድ ላይ ጥብቅ ቁጥጥር ማድረግ ችግሩን ለመፍታት እንደሚያግዝም አመላክተዋል። 

በቀጣይ 10 ዓመታት የቅባት እህሎችን ሙሉ በሙሉ በአገር ውስጥ በማምረት ከውጭ የሚገባውን የድፍድፍ ዘይት ለማስቀረት እቅድ መያዙንም ጠቁመዋል። 

የግብርና ሚኒስትሩ አቶ ዑመር ሁሴን በበኩላቸው አነስተኛ ይዞታ ያላቸው አርሶ አደሮችን በማሰባሰብና ከባህላዊ አመራረት ወደ ዘመናዊ የምርት ዘዴ በማሻገር ችግሩን መቅረፍ እንደሚቻልም ገልጸዋል።

በ10 ዓመቱ የግብርና መሪ እቅድ በምርምርና በቴክኖሎጂ በመታገዝ የተሻሻሉ የቅባት እህል ምርቶችን በማቅረብ ችግሩን ለመፍታት ይሰራልም ነው ያሉት።

በሰፋፊ የመስኖ ልማት የሚሰሩ ባለሃብቶችን በስፋት ወደ ስራ በማስገባት ችግሩን መቅረፍ እንደሚቻልም ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም