ኢትዮጵያ ለአፍሪካ ቀንድ ሰላምና ደህንነት እያበረከተች ያለውን አስተዋጽኦ የሚደነቅ ነው--ዶ/ር ሙኒራ አል ከሊፋ - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ ለአፍሪካ ቀንድ ሰላምና ደህንነት እያበረከተች ያለውን አስተዋጽኦ የሚደነቅ ነው--ዶ/ር ሙኒራ አል ከሊፋ
ሰኔ 21/2013 (ኢዜአ) ኢትዮጵያ ለአፍሪካ ቀንድ ሰላምና ደህንነት እያበረከተች ያለውን አስተዋጽኦ የባህሬን የዲፕሎማሲ ኢንስቲትዮት ዳይሬክተር ዶክተር ሙኒራ አል ከሊፋ አደነቁ።
በባህሬይን የኢትዮጵያ ቆንስል ጄነራል አምባሳደር ጀማል በክር ከባህሬን የዲፕሎማሲ ኢንስቲቲዩት ዳይሬክተር ዶ/ር ሙኒራ አል ከሊፋ ጋር በሁለትዮሽና ቀጠናዊ ጉዳዮችን በትብብር ለመሰራት በሚቻልበት ዙሪያ ውይይት አድርገዋል፡፡
በዚህ ወቅት አምባሳደር ጀማል ኢትዮጵያ ለአፍሪካ ቀንድ፤ ለአፍሪካ እና ለዓለም ሰላም መከበር እያበረከተች ያለውን አስተዋጽኦ እንዲሁም አካባቢያዊ ትስስርን ለማጠናከር እየተጫወተች ያለውን ሚና በተመለከተ መግለጻቸው ተነግሯል፡፡
አምባሳደር የሁለቱን አገራት ትስስር ለማጠናከር በተለይም የእውቀት ሽግግር፤ የዲፕሎማት ስልጠናዎችና ጥናትና ምርምር ዙሪያ ከአቻ የኢትዮጵያ የውጭ ግንኙነትና አገልግሎት ማሰልጠኛ ተቋም ጋር በቅንጅት እንዲሰሩ ጥያቄ አቅርበዋል፡፡
የባህሬን የዲፕሎማሲ ኢንስቲትዮት ዳይሬክተር ዶ/ር ሙኒራ አል ከሊፋ በበኩላቸው ኢትዮጵያ ለአፍሪካ ቀንድ ሰላምና ደህንነት እያበረከተች ያለውን አስተዋጽኦ አድንቀዋል።
የአፍሪካ ቀንድና የመካከለኛው ምስራቅ ትስስር ይበልጥ እንዲጠናከር የዲፕሎማቲክ ተቋማት ትስስር ወሳኝ መሆኑን ዳይሬክተሩ ገልጸዋል፡፡
ስለሆነም በቀጣይ ከኢትዮጵያ የውጭ ግንኙነትና አገልግሎት ማሰልጠኛ ኢንስቲቲዩት ጋር በመሆን በዲፕሎማት አቅም ግንባታ፤ የጋራ ምርምር፤ የቋንቋ ስልጠና እና የተለያዩ ኢኒሼቲቮችን አብሮ ለመስራት ዝግጁ መሆናቸውን ገልጸዋል ሲል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር መረጃ ያሳያል።