ቀጥታ፡

በመዲናዋ የአገልግሎት አሰጣጥን ለማቀላጠፍ በራስ አቅም 'ሶፍትዌሮችን' ማልማት ላይ ትኩረት አድርገን እየሰራን ነው--አቶ ዣንጥራር አባይ

አዲስ አበባ ሰኔ 21/2013 (ኢዜአ) በመዲናዋ ያለውን የአገልግሎት አሰጣጥ ለማቀላጠፍ በራስ አቅም 'ሶፍትዌሮችን' ማልማት ላይ ትኩረት አድርገን እየሰራን ነው ሲሉ በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የአገልገሎት ሰጪ ተቋማት አስተባባሪ ዣንጥራር አባይ ተናገሩ።

ምክትል ከንቲባው ከኢዜአ ጋር በነበራቸው ቆይታ እንደገለጹት አዲስ አበባን እንደ ስሟ አዲስ፤ለኑሮ ምቹና ተስማሚ ለማድረግ ከተማ አስትዳደሩ አዳዲስ አሰራሮችን በመቅረጽ እየተገበረ ይገኛል።

በዚህም በየዘርፉ አንጻራዊ ለውጦችን በሚዘገቡም አሁንም በቂ ምላሽ የሚሹ ማነቆዎች መኖራቸውን ጠቁመዋል።

በመዲናዋ ነዋሪዎቹ በስፋት ከሚነሷቸው ችግሮች መካከል የአገልግሎት አሰጣጥ ችግር ዋነኛው መሆኑንም ነው የተናገሩት።

ይህም ተገልጋዩን ለእንግልት የዳረገና ለብልሹ አሰራር በር የከፈተ ውስብስብ ችግር መሆኑን አንስተው፤ ቴክኖሎጂን በመጠቀም ችግሩን ለመፍታት 'ሶፍትዌር' የማልማት ስራ እየተከናወነ መሆኑን ተናግረዋል።

ቴክኖሎጂን በመጠቀም የአገልግሎት እየሰጡ ባሉ ክፍለ ከተሞች ችግሩን ከመቅረፍ አንጻር በሚፈለገው ደረጃ ባይሆንም መሻሻሎች መኖራቸወንም ምክትል ከንቲባው ተናግረዋል።

ነገር ግን አገልግሎት በሚሰጡ ባለሙያዎች ዘንድ ቴክኖሎጂን በሚፈለገው ደራጃ የመጠቀም አቅም ውስንነት ይታያል ነው ያሉት።

ችግሩን ለመቅረፍም ባለሙያዎችን የማብቃትና ቴክኖሎጂን የማላመድ ስራዎች በስፋት እየተከናወኑ መሆኑን አብራርተዋል።

የዲጅታል መታወቂያ አሰራር በመዘርጋት የወሳኝ ኩነት፣ የልደትና የጋብቻ የምስክር ወረቀት አሰጣጥ ላይ የሚታየውን ችግር ለመቅረፍ ጥረት እየተደረገ መሆኑንም አንስተዋል።

ነገር ግን አሁንም ቢሆን አገልግሎቱን ለማገኘት ለቀናት ብሎም ለወራት የሚመላለሰው የህዝብ ቁጥር ቀላል የሚባል አይደለም ነው ያሉት።

የወሳኝ ኩነት፣ የልደትና የጋብቻ የምስክር ወረቀት በመንግስት ለሚከናወኑ የተለያዩ ተግባራት ወሳኝ ሚና ስላላቸው ቅድሚያ ተሰጥቶ ሊሰራበት እንደሚገባም አስገንዝበዋል።

በጉዳዩ የተሻለ አፈጻጸም ያስመዘገቡ ወረዳዎችን 'ስማርት' ብሎ በመሰየም ልምዳቸውን ለሁሉም ወረዳዎች እንዲያካፍሉ እንደሚደረግም ተናግረዋል።

የንግድ ፍቃድ አገልግሎት፣የኢንቨስትመንት፣የመብራት፣የውኃና የደረቅ ቆሻሻ አገልግሎቶችን በአንድ ቋት በማስተሳሰር በአጠረ ጊዜ ምላሽ ለመስጠት ጥረት መደረጉንም አክለዋል።

ይሁን እንጂ የመብራትና የውኃ አገልግሎትና የክፍያ ስረአቱ ከባንኮች ጋር ተሳስሮም ቢሆን ጥራቱን በጠበቀ መልኩ እየተከናወነ አለመሆኑን ጠቅሰዋል።

አሰራሩን ለማዘመን ከባንኮቹ በተጨማሪ በእያንዳንዱ የመብራት ኃይል ዲስትሪክት ይህንን ብቻ የሚሰሩ ማዕከላት እንደሚቋቋሙ ተናግረዋል።

በሌላ በኩል ከካርታ አሰጣጥ፣ የመሬት ምዝገባና አስተዳደር ጋር የተያያዙ ችግሮች ረዠም ጊዜያትን ያስቆጠሩ በመሆናቸው ችግሩን ለመፍታት ጊዜ መውሰዱን ገልጸዋል።

የከተማ አስተዳደሩ ዲጅታል አሰራርን በማስፋፋት በዘርፉ የሚሰጠውን አገልግሎት ለማዘመንና የሚነሱ ችግሮችን ለመቅረፍ እየሰራ መሆኑንም ነው ምክትል ከንቲባው የተናገሩት።

እንደ ምክትል ከንቲባው ገለጻ በአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ኤጀንሲ አማካኝነት የአገልግሎት አሰራርን የሚያቀላጥፉ "ሶፍት ዌሮችን" የማልማት ስራ አህጽኖት ተሰጥቶት እየተከናወነ መሆኑንም አንስተዋል።

ይህን መልካም ጅማሮ በማጠናከር በየዘርፉ የሚነሱ የአገልገሎት አሰጣጥ ችግሮች የማቃለል ስራ እንደሚከናወንም ክትል ከንቲባው ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም