ቀጥታ፡

የፖለቲካ ፓርቲዎች ህግን አክብረው በመንቀሳቀስ ለምርጫው ሰላማዊነት አስተዋጻ አድርገዋል-የፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት

አሶሳ ሰኔ 21 / 2013 (ኢዜአ) በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል በ6ኛው ጠቅላላ ምርጫ የተሳተፉ የፖለቲካ ፓርቲዎች ህግን አክብረው በመንቀሳቀስ የምርጫው ሂደት ሰላማዊ እንዲሆን አስተዋጾ ማድረጋቸውን የክልሉ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት አስታወቀ፡፡

"ፓርቲዎቹ በምርጫው ሂደት ያሳዩት ተሳትፎ በሀገሪቱ የዴሞክራሲ ባህል እያደገ መምጣቱን ያመላከተ ነው" ሲል ምክር ቤቱ ገልጻል።

የምክር ቤቱ ሰብሳቢ አቶ ካሚል ሃሚድ ለኢዜአ በሰጡት መግለጫ  በክልሉ በ6ኛው ጠቅላላ ምርጫ ሰባት ሃገር አቀፍና ክልላዊ ፓርቲዎች ተሳትፈዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትህ ፣ የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት፣ ብልጽግና፣ የቤንሻንጉል ህዝብ ነጻነት ንቅናቄ፣ የቦሮ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ፣ የአማራ ብሄራዊ ንቅናቄና እናት ፓርቲዎች በምርጫው መሳተፋቸውን ጠቅሰዋል።

የጸጥታ ስጋት ካለባቸው የክልሉ አካባቢዎች በስተቀር ፓርቲዎቹ ትላልቅ የድጋፍ ሰልፎችን በገጠርና በከተሞች ጭምር በመጥራት ዓላማቸውን ለህብረተሰቡ ማስተዋወቃቸውን ተናግረዋል።

ፓርቲዎቹ ከምርጫ ቅስቀሳ አንስቶ ጊዜያዊ የምርጫ ውጤት በየምርጫ ጣቢያው እስኪለጠፍ ሲከተሉት የነበረው መንገድ የምርጫ ስነ-ምግባር እና ደንብ ያከበረ እንደነበር ሰብሳቢው አስረድተዋል፡፡

በቅስቀሳው ሂደት ከተከሰቱ የፖስተር መቀደድን የመሳሰሉ ጥቃቅን ችግሮች በስተቀር ለምክር ቤቱ የቀረበ ቅሬታ እንደሌለ ሰብሳቢው ጠቁመው ቅሬታውን ከጸጥታ አካላት ጋር በመቀናጀት በወቅቱ መፍታት መቻሉን ጠቁመዋል፡፡

በተለይ ፓርቲዎቹ እስከ ሰኔ 8 ቀን 2013 ዓ.ም. ባካሄዱት ቅስቀሳ  በሚያስተላልፉቸው መልዕክቶች   ከቃላት አጠቃቀም ጀምሮ ጥንቃቄ የተሞላበት እንደነበር አስታውሰዋል፡፡

ፓርቲቹ የነበራቸው አጠቃላይ እንቅስቃሴ ህግን ያከበረ በመሆኑ ምርጫው በሠላም እንዲጠናቀቅ አበርክቷቸው የላቀ እንደነበር አመልክተዋል ።

"ፓርቲዎቹ በምርጫው ሂደት ያሳዩት ተሳትፎ በሀገሪቱ የዴሞክራሲ ባህል እያደገ መምጣቱን ያመላከተ ነው" ሲሉ ሰብሳቢው አስታውቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም