ቀጥታ፡

በኢትዮጵያ የሚካሄደው ከ23 ዓመት በታች የምስራቅና መካከለኛው አፍሪካ እግር ኳስ ውድድር ተራዘመ

ሰኔ 21/2013 (ኢዜአ) በኢትዮጵያ የሚካሄደው ከ23 ዓመት በታች የምስራቅና መካከለኛው አፍሪካ እግር ኳስ ውድድር የሚጀመረበት ቀን በ15 ቀናት መራዘሙን የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ጽህፈት ቤት አስታወቀ።

የጽህፈት ቤቱ ኃላፊ አቶ ባህሩ ጥላሁን እንዳሉት ውድድሩ ከሰኔ 26 እስከ ሐምሌ 11 ቀን 2013 ዓ.ም በባህርዳር ስቴዲዬም ለማካሄድ መርሃ ግብር ወጥቶለት ነበር።

ይሁንና የአፍሪካ እግር ኳስ ኮፌዴሬሽን /ካፍ/ ለውድድሩ የሚያደረገውን የገንዘብ ድጋፍ  ባለመልቀቁ ምክንያት ውደድሩ የሚጀመረበት ቀን መራዘሙን ጠቁመዋል።

አንዳንድ ሀገራት በአረብ ሊግ ውድድር ላይ እየተሳተፉ መሆናቸውና በኮቪድ ምክንያት የጉዞ እገዳ ያደረጉ አገራት መኖራቸውም ለውድድሩ መራዘም ተጨማሪ ምክንያት መሆኑን አክለዋል።

ለሁለት ሳምንት ያህል የተራዘመው ይህ ውድድር ከሐምሌ 10 ቀን 2013 ዓ.ም ጀምሮ ለሁለት ሳምንት ያህል በባሕርዳር ስታዲዬም እንደሚካሄድ ገልጸዋል።

ከ23 ዓመት በታች የምስራቅና መካከለኛው አፍሪካ /ሴካፋ /ብሔራዊ እግር ኳስ ቡድን ውድድር 11 አባል አገራትና አንድ አገር ደግም በተጋባዥነት ይካፈሉበታል ተብሎ ይጠበቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም