ጎንደር ዩኒቨርሲቲ 3 ሺህ 500 አዲስ ተማሪዎችን ለመቀበል ተዘጋጅቷል

ጎንደር ሰኔ 21/2013 ( ኢዜአ) የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ''አንድ ተማሪ ለአንድ ቤተሰብ'' ፕሮጀክትን ታሳቢ በማድረግ 3 ሺህ 500 አዲስ ተማሪዎችን ለመቀበል ዝግጅት ማድረጉን አስታወቀ።

ዩኒቨርሲቲው በሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር በኩል ከመላ ሀገሪቱ የተመደቡለትን አዲስ ተማሪዎች በዚህ ሳምንት ለመቀበል ዝግጅት ማጠናቀቁን ገልጻል፡፡

የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ዶክተር አስራት አፀደወይን ለኢዜአ እንዳሉት በሃገር አቀፍ ደረጃ ሞዴል የሆነውን የቤተሰብ ፕሮጀክት በዩኒቨርስቲው ባለፉት ሁለት ዓመታት መተግበሩን አውስተዋል።

የቤተሰብ ፕሮጀክቱን ለማጠናከር በጽህፈት ቤት ደረጃ እንዲዋቀር መደረጉን ተናግረዋል።

ፕሮጀክቱ ተማሪዎችን እርስ በእርስ ከማቀራረብ ባለፈ ወላጆች በዩኒቨርሲቲውና በጎንደር ከተማ ህዝብ እምነት እንዲያሳድሩ ምቹ ሁኔታ መፍጠሩን አመልክተዋል፡፡

ፕሮጀክቱ ባለፉት ሁለት አመታት ወደ ዩኒቨርሲቲው የመጡ 1ሺ 500 የመጀመሪያ አመት ተማሪዎች በከተማው እንደ ወላጅ የሚንከባከባቸውና የሚደግፋቸው አንድ ቤተሰብ እንዲኖራቸው ያስቻለ ትስስር መፍጠሩን ፕሬዘዳንቱ ገልጸዋል፡፡

"ተማሪዎቹ ከመሰረቷቸው ቤተሰቦች ጋር በዓልን አብረው በማሳለፍ ፍቅር ከማግኘት ጀምሮ ለእረፍት ወደ መጡባቸው አካባቢዎች ሲመለሱ የአውሮፕላንና የአውቶብስ የትራንፖርት ወጭ ተችለው በመሸኘት ቤተሰባዊ ትስስር መፍጠር ችለዋል" ብለዋል፡፡

ዩኒቨርሲቲው በዚህ ሳምንት የሚቀበላቸውን አዲሰ ተማሪዎች በተመሳሳይ ሁኔታ በቤተሰብ ፕሮጀክቱ እንዲታቀፉ ለማድረግ በከተማው ፍቃደኛ የሆኑ ወላጆችን የመመልመል ስራ መጀመሩን ተናግረዋል፡፡

ዩኒቨርሲቲው ቁጥራቸው 3ሺ 500 የሚደርሱ አዲስ ተማሪዎችን ከሰኔ 23 ቀን 2013 ዓም ጀምሮ ለመቀበል አስፈላጊውን ዝግጅት ማድረጉን አመልክተዋል።

ወደ ዩኒቨርሲቲው የሚመጡ አዲስ ተማሪዎች ምንም አይነት እንግልት እንዳይደርስባቸው የተለያዩ ኮሚቴዎች ተዋቅረው ወደ ስራ መግባታቸውን አስረድተዋል፡፡

የተማሪዎች ህብረትን ጨምሮ የተማሪዎች የቅበላ፣ የትራንስፖርትና የመስተንግዶ ኮሚቴዎች ተቋቁመው የመማር ማስተማር ስራውን ለማስጀመር የሚያግዙ የትምህርት ግብአቶች ዝግጅት መጠናቀቃቸውን ገልጸዋል፡፡

አዲሶቹ ተማሪዎቹ ወደ ዩኒቨርሲቲው ከገቡ በኋላ የሕይወት ክህሎት ስልጠናን ጨምሮ የዩኒቨርሲቲውን ህጎችና የስነ-ምግባር ደንቦች እንዲያወቁና እንዲገነዘቡ የሚያስችሉ መድረኮች እንደሚከናወኑ ፕሬዝዳንቱ አስታውቀዋል።

ባለፈው አመት ዩኒቨርሲቲው ባቀረበላቸው ጥያቄ መሰረት አንድ ተማሪ በመቀበል ቤተሰባዊ ግንኙነት መመስረት እንደቻሉ የተናገሩት ደግሞ የጎንደር ከተማ ነዋሪ ወይዘሮ እቴናት ወርቁ ናቸው፡፡

ሌላው የከተማው ነዋሪ አቶ መኩሪያው አለሙ በበኩላቸው የዩኒቨርሲቲው የቤተሰብ ፕሮጀክት የጎንደር ከተማን ህዝብ መልካም ስምና እንግዳ ተቀባይነት የሚያጎለብት በመሆኑ አንድ ተማሪ በመረከብ እንደ ወላጅ ለመንከባከብ ፍቃደኛ ሆነው እየተጠባበቁ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

የጎንደር ዩኒቨርሲቲ አሁን ላይ በመደበኛና ተከታታይ መርሀ ግብር ከ35 ሺህ በላይ ተማሪዎችን ተቀብሎ እያስተማረ መሆኑ ታውቋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም