ቀጥታ፡

በአዲስ መንፈስ…

ሚፍታህ አህመድ (ኢዜአ)

ዜጎች ዴሞክራሳዊ መብታቸውን ከሚያረጋግጡበት መንገዶች መካከል የሚፈልጉትን  አስተዳዳሪ በምርጫ መምረጥ ነው።

በዚህም ስድስተኛው ጠቅላላ   ምርጫ  በርካታ ሂደቶችን አልፎ  ሰኔ 14 ቀን 2013 ዓም  በአብዛኛው የሀገሪቱ  ክፍሎች የተካሄደ ሲሆን ከትግራይ ክልል ውጭ ቀሪዎቹ  በመጪው ጷግሜ  1 ቀን 2013  ቀነ ተቆርጧል፡፡

ዘንድሮ የተካሄደው ምርጫ በዜጎች ዘንድ ከፍተኛ  ስጋትና ተሰፋ  የታየበት ነው፡፡ ለዜጎች ስጋት ምክንያት የሆነው ዋናውና ትልቁ  ጉዳይ  የኮቪድ -19   በአለም አቀፍ ደረጃ መከሰቱና የፈጠረው ጫና ቀዳሚውን  ቦታ ይወስዳል፡፡እንደሚታወቀው ኮቪድ- 19 በተከሰተበት ወቅት የአለም ፖለቲካ አለመረጋጋት የሚታይበትና  ወደ ውጥንቅጥ እየገባ የነበረበት ወቅትም ነበር፡፡

ለአብነት የቻይና እና የአሜሪካ ቅራኔ በከፍተኛ ሁኔታ አድጎ ወደ 'ቀዝቃዛ ጦርነት'   ውስጥ  የገቡበት፤  የታዳጊ አገርን ኢኮኖሚና ፖሊቲካ እንደ ካሮት ስር ቁልቁል የወርደበት ወቅት ነበር፡፡  በተመሳሳይ ሁኔታ በአገራችን የኮቪድ -19  ቫይረስ መከሰት ህዝብና መንግስት በከፍተኛ ሁኔታ  ስጋት ውስጥ  ከቶቻው ነበር፡፡  በወቅቱ የመንግስት የስራ ኃላፊዎች የሚሰጡት መግለጫዎች ለአስተዋለ  ስጋታቸውንና  የችግሩን  ግዝፈት  በቀላሉ መረዳት ይችላል፡፡ በተፈጠረውም  መደናገጥ  ለሁለት ሳምንት ያህል ድፍን ኢትዮጵያዊ  ቤት  ዘግቶ እስከመዋል  ድረሶ  እንደነበር  ይታወቃል ፡፡ በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ እንዲሉ  የአንበጣ መንጋ  ወረርሽኝ  ያደረሰው ጉዳት  ቀላል አልነበረም፡፡ ህዝብና መንግስት እረፈት ነሳ፤ የምጥ ጭንቅም ፈጠሮ እንደነበረም  ይታወሳል፡፡

አንዳንድ ፖለቲከኛና  የማህበረሰብ አንቂ (አክቲቪስቱ)  ልዩነቶችን ለጊዜው  በማቆየት  ያጋጠሙ  አለምአቀፍና አገራዊ ችግሮችን  በመቋቋም ዜጎች የገጠማቸውን ችግር በመረዳዳትና  በመተሳሰብ  እንዲያልፉ  ታሪካዊ  ጥረት  ያደረጋሉ ተብሎ በህዝብ ዘንድ ሲጠበቅ  የህዝቦች አይነኬ ማንነቶች በመጠቀም አንዳንድ  ፖለቲከኞችና አክቲቪስቶች   ከሚገባው በላይ በተቃርኖ አቅጣጫ መጓዝ ን የመረጡበት  አጋጣሚ ይታወሳል፡፡  

ይሄም ሌላው ተስፋ  የተደረገው የአዲሱ  የኢትዮጵያን የዴሞክራሲ  ጀምበር  ዳገት  አድርጎታል ማለት ይቻላል ፡፡  በማይገመት ሁኔታ  ሰዎች በተለያዬ መልኩ  ክቡር የሆነውን ህይወታቸውን የሚያጡበት ፤  ዜጎች የአካል ጉዳትና ለመጥፎ ስነልቦና  ጠባሳ የሚጋለጡበት፣ በብዙ ሚሊዮን  ግምታዊ ዋጋ ያለው የአገርና የ ዜጎች ንብረቶች  የወደመበት    ኢኮኖሚያዊ ማህበራዊና ፖለቲካዊ ቀውስ  ፈጥሮ አልፏል፡፡

ሌላው ትልቁ  ሁኔታ  አሸባሪው የህወሃት ቡድን  አሳታፊ  ውይይት ተደርጎበት፣ በፌዴሬሽንና በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤቶች  ውሳኔ  እስከ አንደ አመት ጊዜ እንዲራዘም  የተወሰነውን  6ኛው አገራዊ  ምርጫ  ውሳኔ በማን አለብኝነት በመጣስና  በህገ መንግስቱ  ምርጫን የማስፈጸም ብቸኛ  ስልጣን ከተሰጠው  የኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ  ዕውቅና  ውጭ ህገወጥ ምርጫ አካሄደ፡፡

በዚህ ሳያበቃ ከ200 ሺ በላይ  ልዩ ሃይል አሰልጥኖ   የዜጎችንና የአገርን  ህልውና አደጋ ውስጥ በሚከት መልኩ ዝግጅት ከማድረግ ባለፈ  በሀገር ህልውና ላይ ጉዳት የማድረግ ሂደት ውስጥ ገባ ፡፡ የሚያካሂደውን አንዳንድ ትንኳሳዎችና የህግ ጥሰቶችን መንግስት በመታገስ ወደ ግጭት ላለመግባት በትዕግስት ቢያሳልፍም ፤ በወረሃ ጥቅምት  ከ20 አመታት በላይ የትግራይ ህዝብ ከማንኛውም ጥቃት ሲጠብቅ የኖረውን በሀገር መከላከያ ሰራዊት የሰሜን ዕዝን  ባልታሰበ ሁኔታ ጀርባውን በመውጋትና  ጥቃት በመፈጽም  ታሪክ የማይረሳው ክህደት  የፈጸመበት ነበር፡፡ በዚህም ምክንያት በማይካድራ  እና በሌሎች ቦታዎች የጅምላ ግድያ በአሰቃቂ ሁኔታ ተፈጸመ፡፡

 በውስጥ የተፈጠረው ይህንን የመሳሰሉና ከዚሁ ጋር ግንኙነት ያላቸው ሌሎች የሰላም ችግሮን በመጠቀም በርካታ ባዕድ ሀገራት ፍላጎታችውን ለማስፈጸም ከፍተኛ ጫና በኢትዮጵያ ላይ ለማሳደር  እንደመልካም አጋጣሚ በመቁጠር ርብርባቸውን ጀመሩ፡፡ ሉአላዊ ድንበርን አልፎ  እስከመውረር ፤  የውሃ ሀብትን በጋራ የመጠቀም መርህን በማንገብ ብሎም በራስ  የገንዘብ  ወጭ የሚገነባን  የህዳሴ ግደቡ አቁሙ እስከማለት ጫና ለማድረስ ሞክረዋል። ይህን ጉዳይ በወጉ  የተረዳው   ኢትዮጵያዊ 6ኛው አገራዊ ምርጫ በሰላማዊ መልኩ ተፈጸሚነቱ ላይ ስጋትና ተስፋ የፈጥረ ነበር፡፡

 ምንም እንኳን ስጋት ቢያድረበትም በውስጥና በውጭ የተፈጠረው ጫና እውነትነት የጎደለው፤ የአገር ሉዓላዊነትን የመጻረር አዝማሚያ መሆኑን በመረዳቱ  ምርጫውን በጽናት ለመካሄድ ሙያ ብልብ ነው በሚል ቢሂል ወቅትና ጊዜውን በጉጉት ሲጠብቅ ቆይቶ ለአለም ህዝብ በሚያስተምር መልኩ ምርጫውን እንዳካሄደ  በመታዘብ የተሳተፉ ቡድኖች ጭምር አረጋግጠዋል፡፡

በምርጫውም እለት ዴሞክራሲያዊ መብቱን ከመጠቀም በተጨማሪ  በርካታ ሚሊዮን ችግኝ  በመትከል የአረንጓዴ አሻራውን  ለሀገሩ አሳርፏል፡፡ እርስ በርስ ይጫረሳሉ ብለው የተመኙ  የውጭ ሃይሎችንም  ተሰፋ አስቆርጠ፡፡

ዜጎች በቀጥታ ባደረጉት ተሳትፎ የድህነትና የደህንነት ችግር በመቅረፍ የአገሪቱን ሁለንተናዊ ዕድገት ያረጋግጣል ላሉት ፓርቲ አስቸጋሪ ሁኔታ በመቋቋም በትዕግስት ተወካዮቻቸውን ምርጠው አሳይተዋል፡፡ በሰኔ 14 የተካሄደው ምርጫ  ለ445 የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መቀመጫዎችን ለማግኘት የፊታችን ጳጉሜን 1 2013 ዓም የሚካሄደውን ምርጫ ጨምሮ  47 የፖለቲካ ፓርቲዎች 8ሺህ 209 ዕጩዎችን አቅርበው በአገር አቀፍ  የምርጫ ክልሎች ላይ  ተወዳድረዋል፡፡ ከፓርቲዎች በተጨማሪ 125 የግል ተወዳዳሪዎች በዕጩነት ቀርበዋል ተወዳድረዋል፡፡ ከነዚህ  ውስጥ አሸናፊ የሆኑት  በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ህዝብን ወክለው ይገባሉ፡፡

እነዚህ ወኪሎች ለኢትዮጵያም ብቻ ሳይሆን ለቀጠናው አገራት መተሳሳር ትልቅ አደራ ተጥሎባቸዋል። የአሜሪካ የሰላም ኢንስቲትዮት በኢትዮጵያ  በሚካሄደው ስድስተኛው ምርጫ   37ሚሊዮን 408 ሺህ 6መቶ  ሰዎች ድምጽ ለመስጠት የተመዘገቡ መሆኑን ጠቅሶ ምርጫው  ሊሳካ  እንዳማይችል  ያደረገው ትንበያንም ያመከነ ምርጫ ነው ማለት ይቻላል፡፡

ከኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ ያገኘነው መረጃ እንደሚያሳየው ደግሞ 6ኛዉ ሀገራዊ ምርጫ 45 የአገር ውስጥ እና ሶስት አለም አቀፍ የምርጫ ታዛቢዎች  የታዘቡበት ነው፡፡

ታዛቢዎቹም ከልምድ ማነስ የተነሳ ጥቃቅን ችግሮች ከማጋጠማቸው ውጭ  ምርጫው  ሰላማዊ፣ ፍትሃዊና ዲሞክራሲያዊ በሆነ መንገድ መጠናቀቁን ያረጋገጡት እውነትና  ሁነት  ሆኖ  ማለፉን ማረጋግጣቸውን  ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ  ይፋ አድርገዋል።

ከዚህ በመነሳትም በቀጣይም  የሚካሄድ   ምርጫ አሁን የታዩ ችግሮችን በመቅረፍ የተሳካ  ምርጫ ኢትዮጵያ  እንደምታካሂድ አለም የተገነዘበ  መሆኑን  መናገር የሚያስችል ሆኗል ፡፡የኢትዮጵያ ህዝቡም እምነትና ተስፋ አሳድሯል፡፡

 ከዚህም ጎን ለጎን ሁለተኛው ዙር የታለቁ  የኢትዮጵያ  ህዳሴ ግድብ የውሃ ሙሌትን  በቅርቡ በስኬት እንደሚጠናቀቅ ዜጎች በጉጉት እየጠበቁ  ይገኛሉ፡፡

እነዚህ  ሁለት አበይት ጉዳዮች  በኢትዮጵያዊያን  ተስፋ ላይ ከፍተኛ  መነሳሳት የሚፈጥር ሲሆን ፤ የኢትዮጵያን ውድቅት ለሚመኙ  የውስጥና  ውጭ  ጠላቶች  ግን  ከፍተኛ  የሞራል  ውድቅት  እንደሚያስከትል  ያለጥርጥር መገመት ይቻላል፡፡

 እነዚህ አበይት ሁነቶች    አልፈው  በአዲስ  አመት  ዋዜማ  የሚመሰረተው አዲሱ መንግስት በአዲስ መንፈስ የአገሪቱን ሰላምና ደህንነት በአስተማማኝ መሰረት ለመረጋገጥ ተግቶ እንደሚሰራና  የኢትዮጵያን  የዴሞክራሲና ብልጽግና   ወደ  ሚያረጋግጥ ከፍታ ላይ የሚያደረስ የብርሃን ፍንጣቂ የሚታየበት አመት እንዲሚሆን  ከ6ኛው ጠቅላላ ምርጫ  ማግስት ጀምሮ ዜጎች  በተስፋ ተሞለተው የሚጠባበቁት  ጉዳይ  ሆኗል፡፡ለዚህም ‘’ሁሉም ቢተባበር ቢጥር  …’’ የሚለውን  ዜማ  በመጋበዝ ተሰናበትኳችሁ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም