በገጠር የሚተከሉ ችግኞች የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ እያገዙ ነው---የድሬዳዋ ግብርና ቢሮ - ኢዜአ አማርኛ
በገጠር የሚተከሉ ችግኞች የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ እያገዙ ነው---የድሬዳዋ ግብርና ቢሮ
ድሬዳዋ ሰኔ 20/2013 (ኢዜአ/) በየዓመቱ የሚተከሉ የቅይጥ የደንና የፍራፍሬ ችግኞች በቤተሰብ ደረጃ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ አበርክቷቸው የጎላ መሆኑን የድሬዳዋ አስተዳደር ግብርና፣ ውሃ፣ ማዕድንና ኢነርጂ ቢሮ አስታወቀ።
“ኢትዮጵያን እናልብሳት” በሚል መሪ ሃሳብ እየተካሄደ ባለው የአረንጓዴ አሻራ መርሀ ግብር ከ200 በላይ የድሬዳዋ አስተዳደር የመንግስት ሠራተኞች በገጠር ቀበሌ ተገኝተው በወጣቶች ማሳ የደንና የፍራፍሬ ችግኞችን ተክለዋል፡፡
በችግኝ ተከላ መርሃ ግብሩ ላይ የተገኙት የድሬዳዋ ግብርና፣ ውሃ፣ ማዕድንና ኢነርጂ ቢሮ ኃላፊ አቶ ኢብራሂም ዩሱፍ ለኢዜአ እንዳሉት በክረምቱ ኢትዮጵያን እናልብሳት በሚል መሪ ሃሳብ በገጠርና በከተማ 2 ሚሊዮን ችግኞች ይተከላሉ፡፡
የዛሬውን ጨምሮ በየዓመቱ የሚተከሉት የፍራፍሬና የደን ችግኞች ጎርፍን ከመከላከል ባለፈ በቤተሰብ ደረጃ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ ወሳኝ አበርክቶ እንዳላቸው ተናግረዋል።
ባለፉት ዓመታት የተተከሉ የፓፓያ ችግኞች ምርት በመስጠት ለአርሶ አደሩ ልጆች የሥራ እድል እየፈጠሩና ተጠቃሚ እያደረጓቸው መሆኑን አቶ ኢብራሂም አስረድተዋል፡፡
በችግኝ ተከላው ላይ የተሳተፉት በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የድሬዳዋ አስተዳደር ንግድ፣ ኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት ቢሮ ኃላፊ አቶ ከድር ጁሃር በበኩላቸው “የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ላይ በተቀናጀ መንገድ በመሳተፍ ድሬዳዋን ከጎርፍ አደጋ ስጋት የመከላከል ተግባርን ውጤታማ ማድረግ ይገባል” ብለዋል።
አስተዳደሩ ለአፈርና ውሃ ጥበቃ ሥራና ለችግኝ እንክብካቤ ልዩ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
“የአፈርና ውሀ ጥበቃ እንዲሁም ችግኝ ተከላና እንክብካቤ በተደጋጋሚ ጎርፍ የሚያደርሰውን ጥፋት ለመታደግ ያግዛል፤ የገጠሩ ማህበረሰብ የምግብ ዋስትናን ያረጋግጣል፤ የድሬዳዋን ሞቃታማ አየር ለኑሮ ተስማሚ ያደርጋል” ብለዋል፡፡
የኢጂአነኒ ገጠር ቀበሌ ወጣቶች ማህበር አስተባባሪ ወጣት መሐመድ ጃቢር በየአመቱ እየተተከሉ ባሉ ችግኞች የማህበሩን አባላት ይበልጥ እንዲተጉ ያነሳሳቸው መሆኑን ገልጿል፡፡
ማህበሩ በ20 ሥራ እጥ ወጣቶች መመስረቱን ጠቁሞ፣ ምድረበዳ የነበረውን አካባቢ ጠንክሮ በመስራት ወደ እርሻ መለወጣቸውን ተናግሯል።
“በጉልበታችን የውሃ ጉድጓድ ቆፍረን አትክልትና ፍራፍሬ በማምረት ህይወታችንን እየለወጥን እንገኛለን” ብሏል፡፡
ባለፉት አመታትየተተከሉ ልዩና ምርጥ የፓፓያ ዛፎች ዛሬ ምርት እየሰጡ መሆናቸውን ተናግሮ ማህበሩ በተጨማሪም ድንች፣ ቃሪያ፣ ሽንኩርና ቲማቲም በማምረት በዓመት እስከ 800 ሺህ ብር ገቢ ማግኘት መጀመሩን ገልጿል፡፡
“የኛን መለወጥ የተመለከቱ የአካባቢው ወጣቶች እየተከተሉን” ሲል አክሏል፡፡
በድሬዳዋ ገጠር ቀበሌዎች አምና በአረንጓዴ አሻራ የተተከሉ የፍራፍሬ እና የዛፍ ችግኞች መካከል 65 በመቶዎቹ መጽደቃቸው ታውቋል፡፡