የትራንስፖርት ሚንስቴር እና ተጠሪ ተቋማት ሰራተኞች 4 ሺህ ችግኞችን ተከሉ - ኢዜአ አማርኛ
የትራንስፖርት ሚንስቴር እና ተጠሪ ተቋማት ሰራተኞች 4 ሺህ ችግኞችን ተከሉ
ሰኔ 20/2013 (ኢዜአ) የትራንስፖርት ሚንስቴር እና ተጠሪ ተቋማት አመራርና ሰራተኞች በዛሬው እለት 4 ሺህ ችግኞችን ተክለዋል።
"ኢትዮጵያን እናልብሳት" በሚል መርህ ዘንደሮ እየተከናወነ ባለው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር የሚኒስቴሩና ተጠሪ ተቋማቱ ሰራተኞች በድምሩ 1 ነጥብ 6 ሚሊዮን ችግኞችን ለመትከል አቅደዋል።
እቅዳቸውን ለማሳካትም በዛሬው እለት ብቻ በምስራቅ ሸዋ ዞን ሎሜ ወረዳ 4 ሺህ ችግኞችን ተክለዋል።
የትራንስፖርት ሚኒስትሯ ዳግማዊት ሞገስ፤ ኢትዮጵያን አረንጓዴ ለማድረግ ችግኞችን መትከልና መንከባከብ የሁላችንም ሃላፊነት ሊሆን ይገባዋል ብለዋል።
ለዚህም የትራንስፖርት ሚኒስቴርና ተጠሪ ተቋማት ሰራተኞች የድርሻቸውን ለመወጣት ትኩረት ሰጥተው ይሰራሉ ብለዋል።
ሁላችንም ተባብረን ኢትዮጵያን ማልማት፣ ስነ ምህዳሯን መጠበቅና አረንጓዴ ማድረግ ይገባናል ብለዋል።
ባለፈው ዓመት የተተከሉ ችግኞችን በመንከባከብ 80 በመቶው እንዲፀድቁ መደረጉን የጠቀሱት ሚኒስትሯ ዘንድሮም የሚተከሉትን የመንከባከቡ ስራ ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።
የፐብሊክ ሰርቪስ ሰራተኞች ድርጅት የኮሙንኬሽን ዳይሬክተር ሰለሞን አምባቸው ችግኞችን በመትከልም በመንከባከብም ኢትዮጵያን ውብና አረንጓዴ ማድረግ የእያንዳንዳችን ሃላፊነት መሆን አለበት ብለዋል።
የአረንጓዴ ልማቱ ከአገራዊ ፋይዳው በተጨማሪ በዓለም አቀፍ ደረጃ ስጋት እየሆነ የመጣውን የአየር ንብረት መዛባት ለመከላከል ወሳኝ መሆኑን ጠቅሰዋል።
በኢትዮጵያ እየተገነቡ ያሉ ግዙፍ የውሃ ሃይል ማመንጫዎች በደለል እንዳይሞሉ ለማስቻልም ችግኞችን መትከልና የአፈር መሸርሸርን መከላከል ለነገ የማይተው ስራ መሆኑን አብራርተዋል።
የኢትዮጵያ ምድር ባቡር ኮርፖሬሽን የባቡር ዘርፍ ምክትል ስራ አስፈፃሚ አቶ በሃይሉ ስንታየሁ፤ የተቋማቸው ሰራተኞች ችግኞችን በመትከልና በመንከባከብ የድርሻቸውን እየተወጡ መሆኑን ገልፀዋል።
ከ2011 ዓ.ም ጀምሮ በኦሮሚያ ክልል ምስራቅ ሸዋ ሎሜ ወረዳ በ200 ሄክታር መሬት ላይ ከ2 ሚሊዮን በላይ ችግኞችን መትከላቸውን አስታውሰዋል።
ከተተከሉት ችግኞች መካከል 92 በመቶው መፅደቃቸውንም ተናግረዋል።
ኢትዮጵያዊያን ከተባበርን የማናሳከው ነገር የለም አገራችንን አረንጓደ ለማድረግ በጋራ እንስራ ያሉት ደግሞ የመንገድ ፈንድ ፅህፈት ቤት ዋና ዳይሬክተር አቶ ራሽድ መሀመድ ናቸው።