የመጠቀሚያ ጊዜያቸው ያለፈና የጥራት ደረጃቸው ዝቅተኛ የሆነ ምግቦች ተወገዱ - ኢዜአ አማርኛ
የመጠቀሚያ ጊዜያቸው ያለፈና የጥራት ደረጃቸው ዝቅተኛ የሆነ ምግቦች ተወገዱ
ጅማ፣ ሰኔ 20 ቀን 2013 (ኢዜአ) ግምታቸው 260 ሺህ ብር የሆነ የመጠቀሚያ ጊዜያቸው ያለፈና የጥራት ደረጃቸው ዝቅተኛ የሆነ የምግብ ሸቀጦች መወገዳቸውን የኢትዮጵያ ምግብና መድሃኒት ቁጥጥር ባለስልጣን አስታወቀ።
የባለስልጣኑ ደቡብ ምእራብ ኢትዮጵያ ጅማ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት የመድሃኒት ባለሙያ ኢንስፔክተር ሚፍታህ ዝናብ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ 86 የምግብ ዓይነቶች ተሰብስበው ተወግደዋል።
የምግብ አይነቶቹ የመጠቀሚያ ጊዜያቸው ያለፈባቸውና ገላጭ ጽሁፍ የሌላቸውና የጥራት ደረጃቸው ዝቅተኛ ሆኖ በመገኘቱ ተሰብስበው እንዲወገዱ መደረጉን ተናግረዋል።
ከተወገዱት ምግቦች መካከል የተለያዩና የታሸጉ ጭማቂዎች፣ ለስላሳ መጠጦች፣ የለውዝ ቅቤና ከረሜላዎች እንደሚገኙበት ጠቅሰዋል።
ህብረተሰቡ ከታሸጉ ምርቶች በተጨማሪ ማርና ቅቤ ላይ ባዕድ ነገር የሚቀላቅሉ ግለሰቦች ስላሉ በጥንቃቄ መሸመት እንዳለበት አስገንዝበዋል።
አጠራጣሪ ሁኔታ ሲያጋጥምም በ8482 ነጻ የስልክ መስመር በመደወል መጠቆም እንደሚቻል ኢንስፔክተሩ አስታውቀዋል።