በመተከል ዞን ወደ አካባቢያቸው ለተመለሱ ተፈናቃይ ዜጎች ሰብአዊ ድጋፍ እየተደረገ መሆኑን የዞኑ አስተዳደር ገለጸ - ኢዜአ አማርኛ
በመተከል ዞን ወደ አካባቢያቸው ለተመለሱ ተፈናቃይ ዜጎች ሰብአዊ ድጋፍ እየተደረገ መሆኑን የዞኑ አስተዳደር ገለጸ
አዲስ አበባ፣ ሰኔ 20 ቀን 2013 (ኢዜአ) በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል መተከል ዞን በነበረው የፀጥታ ችግር ተፈናቅለው ቆይተው ወደ ቀደመ አካባቢያቸው ለተመለሱ ዜጎች ሰብአዊ ድጋፍ እየተደረገ መሆኑን የዞኑ አስተዳደር ገለጸ።
የዞኑ ምክትል አስተዳዳሪ አቶ ጸኃይ ቡየ ከማንዱራ ወረዳ ፎቶ ማንጃሪ ቀበሌ ተፈናቅለው ወደ አካባቢያቸው ለተመለሱ ዜጎች የሰብዓዊ ድጋፍና ሌሎች ማህበራዊ አገልግሎቶችን እንዲያገኙ እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል።
የተፈናቀሉ ዜጎችን ወደ ነበሩበት አካባቢ በመመለስ በዘላቂነት የማቋቋም ስራም በመከናወን ላይ መሆኑን ተናግረዋል።
ሰብአዊ ድጋፍ የማድረግ፣ መሰረተ ልማቶች የማሟላትና የፀጥታ ስጋቶች በዘላቂነት የመፍታት ተግባር እየተከናወነ መሆኑን አረጋግጠዋል።
ኢዜአ ያነጋገራቸው የፎቶ ማንጃሪ ቀበሌ ተመላሾች መንግስት የቤት መስሪያ ቁሳቁስ፣ የእርሻ ትራክተርና ሌሎች ድጋፎችን እያደረገላቸው በመሆኑ አመስግነዋል።
በግጭቱ ወቅት የፈረሱ ጤና ጣቢያዎች፣ ትምህርት ቤቶችና ሌሎችም ማህበራዊ አገልገሎቶች በአፋጣኝ እንዲገነቡም ጠይቀዋል።
የዞኑ የተቀናጀ ግብረ ኃይል ኮማንድ ፖስት ሰብሳቢ ሌተናል ጀኔራል አስራት ዴኔሮን ጨምሮ ከክልል፣ ዞንና ወረዳ የተውጣጡ አመራሮች በስፍራው በመገኘት ተመላሾችን ጎብኝተዋል።
በነበረው የፀጥታ ችግር ከአካባቢው ርቀው ቆይተው ወደ ፎቶ ማንጃሪን ቀበሌ የተመለሱ ዜጎች እየተደረገላቸው ያለውን ሰብአዊ ድጋፍም ሃላፊዎቹ ተመልክተዋል።
ተፈናቅለው የነበሩ ዜጎች እራሳቸውን ችለው በዘላቂነተ እስኪቋቋሙ ድረስ መንግስት የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠውላቸዋል።
የኮማንድ ፖስቱ ሰብሳቢ ሌተናል ጀኔራል አስራት ዴኔሮ የወደሙ ማህበራዊ አገልግሎት ሰጪ ተቋማትን መልሶ ለመገንባት ተቀናጅቶ መስራት እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል። የቀበሌ አስተዳደሮች እና የአገር ሽማግሌዎች ህዝብን የማረጋጋትና ለመጪው ትውልድ ሰላም፣ አብሮነትና አንድነት በትኩረት መስራት እንዳለባቸውም አስገንዝበዋል።