በአገራዊ ምርጫው ድምጽ ከተሰጠባቸው 440 የምርጫ ክልሎች 221ዱ ውጤት አሳውቀዋል... የኢትዮጵያብሔራዊ ምርጫ ቦርድ - ኢዜአ አማርኛ
በአገራዊ ምርጫው ድምጽ ከተሰጠባቸው 440 የምርጫ ክልሎች 221ዱ ውጤት አሳውቀዋል... የኢትዮጵያብሔራዊ ምርጫ ቦርድ
አዲስ አበባ፤ ሰኔ 19/2013(ኢዜአ) በአገራዊ ምርጫው ድምጽ ከተሰጠባቸው 440 የምርጫ ክልሎች 221ዱ ውጤት ማሳወቃቸውን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ገለጸ።
የቦርዱ የኮሙኒኬሽን አማካሪ ሶሊያና ሽመልስ እንደገለጹት ውጤት ካሳወቁት መካከል በኦሮሚያ ክልል የሚገኙ 125 የምርጫ ክልሎች ቀዳሚ ናቸው።
አማራ ክልል 40 አካባቢ የሚሆኑ የምርጫ ክልሎችን ውጤት ማሳወቁም የተገለጸ ሲሆን፤ የሌሎቹ ምርጫ ክልሎች ውጤት መዘግየት ከምርጫ ጣቢያ ወደ ምርጫ ክልል የትራንስፖርት ችግር፣ የድምፅ ቆጠራ ቶሎ አለመጠናቀቅና ከምርጫ ጣቢያ ድምጽ በትክክል ተቆጥሮ አለመቅረብ በምክንያትነት ቀርበዋል።
ከአዲስ አበባ 23 ምርጫ ክልሎች ደግሞ ውጤት ያሳወቁት 10 መሆናቸውን ገልጸዋል።
የጋምቤላና የሲዳማ ክልሎችን ጨምሮ በድምፅ መስጫው ማግስት ሰኔ 15 ምርጫ ከተካሄደባቸው አካባቢዎች በስተቀር ሌሎቹ ዛሬ ውጤቱን ማጠናቀቅ አለባቸው ተብሏል።
በተያያዘ በድሬዳዋ ስድስት ምርጫ ጣቢያዎች ለክልል ምክር ቤት ምርጫ ሳይደረግባቸው መቅረቱን "አሁን አረጋጠናል” ብለዋል የቦርዱ የኮሙኒኬሽን አማካሪ።ለዚህም የክልል ምክር ቤት የምርጫ ወረቀት በቦታው አለመድረሱ በምክንያትነት ተገልጿል።
ለተፈጠረው ችግር ሀላፊነቱን የሚወስደውን አካል ለመለየት የምርጫ ክልሉና የቦርዱ ጽህፈት ቤት እያጣራ ነው ብለዋል አማካሪዋ።
በደቡብ ክልል የቁጫ ምርጫ ክልል የጸጥታ ስጋት ያለበት መሆኑ ስለተረጋገጠ ቦርዱ ሌላ ውሳኔ እስከሚያሳልፍ ድረስ የድምፅ ቆጠራና ድመራ ሂደት እንዲቆም መወሰኑንም ገልጸው፤ ለጊዜው የምርጫ ቁሳቁሶች ታሽገው እንዲቀመጡ መደረጉንም አስታውቀዋል።