በሀይማኖት አባቶች መካከል የወረደው እርቅ ለሀገሪቱ ሰላምና እድገት የጎላ አስተዋጽኦ ይኖረዋል- አገልጋዮች - ኢዜአ አማርኛ
በሀይማኖት አባቶች መካከል የወረደው እርቅ ለሀገሪቱ ሰላምና እድገት የጎላ አስተዋጽኦ ይኖረዋል- አገልጋዮች
ሐምሌ 29/2010 በሃይማኖት አባቶች መካከል የወረደው እርቅ የሀገሪቱን ሰላምና እድገት ለማረጋገጥ የጎላ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው የሃማኖት ተቋማት አገልጋዮች ተናገሩ፡፡ የኢትዮጵያ ወንጌላዊት መካነኢየሱስ ቤተክርስቲያን አገልጋዩ ቄስ ጥላየ ከበደ እንዳሉት በሃይማኖት ተቋማት መካከል የሚፈጠረው ልዩነት በምዕመናኑ መካከል “የሀሳብና የተግባር ልዩነቶችን” ያመጣል፡፡ ይህን መሰሉ ልዩነት በቤተ እምነቶች ሳይወሰን በሀገሪቱ ሰላምና መረጋጋገት ላይም አሉታዊ ተጽዕኖ እንደሚፈጥር ገልጸው በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን የኃይማኖት አባቶች መካከል የወረደው እርቀ ሰላም ምዕመናኑ “በአንድ ልብና መንፈስ” ለአንድ አላማ እንዲተባበሩ በር እንደሚከፍት ተናግረዋል፡፡ ኢትዮጵያውያን በተባበረ ክንዳቸው የሀገራቸውን ሉዓላዊነት ማስጠበቃቸውን ጠቅሰው “የተጎዳዳንበትንና የተበታተንንበትን ዘመን ከታሪክ በመማርና ራሳችን ያበላሸነውንም አስተካክለን” ለሀገሪቱ ሰላምና እድገት “በጋራ መስራት ይገባናል” ብለዋል፡፡ የይቅርታና አንድነት ጅማሮውን ለማስቀጠል የሃይማኖት አባቶች ተከታዮቻቸውን ማስተማርና አርዓያም ሆነው መገኘት እንዳለባቸው የጠቆሙት ቄስ ጥላየ ምዕመናኑም ሃይማኖታዊ አስተምህሮዎችን በመተግበር ለሰላምና አንድነት ቅድሚያ እንዲሰጡ መክረዋል፡፡ `የስክሪፕቹዋል ላይት ባይብል ሶሳይቲ` ዋና ጸሓፊ አቶ ፈቃዱ ቤኛ የሃይማኖት ተቋማት “የደከመውን ማበርታት፣ የፈረሰውን መጠገን፣ የተለያየውንና የተበታተነውን ማዋሃድ ሲገባቸው ራሳቸው መለያየታቸው” ለሀገሪቱም ችግር ሆኖ መቆየቱን ገልጸው አሁን የወረደው እርቀ ሰላም እንዳስደሰታቸው ተናግረዋል፡፡ ምዕመናኑ በመከባበርና በመፈቃቀር የሀገሪቱን ሰላምና እድገት ቀጣይነት ለማረጋገጥ በሚደረገው ጥረት ጠንክረው እንዲሰሩም መክረዋል፡፡ በኢትዮጵያ ወንጌላዊት መካነኢየሱስ ቤተክርስቲያን የሚያገለግሉት ቄስ ጸጋነሽ ከ26 ዓመታት በኋላ በሁለቱ ሲኖዶሶች መካከል በወረደው እርቀ ሰላም ከተደሰቱ አስተያየት ሰጪዎች መካከል አንዷ ናቸው፡፡ በሀገሪቱ እየታየ ያለውን ለውጥ ተከትሎ በስደት የቆዩ አባቶች ወደ ሀገራቸው መመለሳቸውና በሀገር ውስጥ የነበሩ አባቶችም ያደረጉላቸው አቀባበልና ያሳዩዋቸው ልባዊ ፍቅር የተለየ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ በሁለቱ ሲኖዶሶችና በእስልምና ሀይማኖት አባቶች መካከል የወረደው እርቅ ለሀገሪቱ ሰላምና እድገት የጎላ አስተዋጽኦ እንደሚያበረክት ገልጸው እርቀ ሰላሙ እንዲመጣ ከፍተኛ ጥረት ላደረጉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ ምስጋና አቅርበዋል፡፡ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን የገነተ ጽጌ ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን አገልጋዩ መምህሬ ገብረ ወልድ ደመቀ በበኩላቸው በቤተክርስቲያኗ አባቶች መካከል የነበረው መለያየት ተስፋ አስቆራጭ እንደነበር ተናግረዋል፡፡ ትውልዱ አሁን ከወረደው እርቀ ሰላም ይቅር መባባልን፣ ሰላምንና መተባበርን ተረድቶ ለሀገሩ ሰላም፣ አንድነትና ልማት ተግቶ እንዲሰራም መክረዋል፡፡ ሌላው የዚሁ ቤተክርስቲያን አገልጋይ አባ ላዕከማርያም ገብረ ስላሴም በሁለቱ ሲኖዶሶች አንድነት መደሰታቸውን ገልጸው የአንድነቱ ፍጻሜ የሰመረ እንዲሆን የመንፈስ ልጆቻቸውን የማስተማር ኃላፊነታቸውን ለመወጣት ዝግጁ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡ የሁለቱ ሲኖዶሶች የእርቅ ማብሰሪያ ፕሮግራም የኢፌዴሪ ፕሬዝዳንት ዶክተር ሙላቱ ተሸመን ጨምሮ የተለያዩ የሀይማኖት ተቋማት ተወካዮች፣ የመንግሥት የስራ ኃላፊዎችና የእምነቱ ተከታዮች በተገኙበት ትናንት በሚሊኒየም አዳራሽ ተከናውኗል፡፡