በስምጥ ሸለቆ አካባቢ የሚገኙ ሐይቆችን ከደለልና ከብክለት ለመታደግ ከ16 ሚሊዮን በላይ ችግኝ ተከላ ተጀመረ - ኢዜአ አማርኛ
በስምጥ ሸለቆ አካባቢ የሚገኙ ሐይቆችን ከደለልና ከብክለት ለመታደግ ከ16 ሚሊዮን በላይ ችግኝ ተከላ ተጀመረ
ሀዋሳ ሰኔ 19/2013 (ኢዜአ) በስምጥ ሸለቆ አካባቢ የሚገኙ ሐይቆችን ከደለልና ከብክለት ለመታደግ ከ16 ሚሊዮን በላይ ችግኝ ተዘጋጅቶ ተከላው መጀመሩን የፌዴራል ተፋሰሶች ልማት ባለስልጣን አስታወቀ።
በባለስልጣኑ የስምጥ ሸለቆ ሐይቆች ተፋሰስ ልማት ጽህፈት ቤት ከሀዋሳ ከተማ አስተዳደር ጋር በመተባበር የዘንድሮውን አረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብርን በማስመልክት ዛሬ በሀዋሳ አውሮፕላን ማረፊያ አካባቢ የችግኝ ተከላ አካሂደዋል።
በጽህፈት ቤቱ የተቀናጀ ተፋሰስ ልማትና ወንዝ አመራር ዳይሬክተር አቶ ዴቢሶ ዴዴ በወቅቱ ለኢዜአ እንደተናገሩት፤ የሐይቆቹ መገኛ ስፍራዎችን ከብክለትና ከደለል ለመጠበቅ እየተሰራ ነው።
በኦሮሚያ፣ደቡብና ሲዳማ ክልሎች በሚገኙ ሀዋሳ፣ዝዋይ ሻላ፣ አባያ ጫሞ ሐይቆች እና ጨው ባህር አካባቢ የተቀናጀ የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራ ትኩረት መሰጠቱን ጠቁመዋል።
በተለይ በተፋሰሶቹ ላይ አፈርና ውሃ ጥበቃ፣እርከን ስራና ችግኝ ተከላ ከማከናወኑ በተጓዳኝ ስለ አረንጓዴ አሻራ ጠቀሜታ በተፋሰሱ ለሚገኙ የህብረተሰብ ክፍሎች ግንዛቤ የማስጨበት ተግባራት በመከናወን ላይ እንደሚገኝ ጠቅሰዋል።
የዘንድሮ ሀገር አቀፍ ችግኝ ተከላ መርሃ ግብርን መሠረት በማድረግም 16 ሚሊዮን 300 ሺህ ችግኝ ተዘጋጅቶ በተፋሰሶቹ አካባቢ ተከላው መጀመሩን አስታውቀዋል።
ይህም ተፋሰሶቹን ከብክለትና ጥፋት ከመታደግ ባለፈ የውኃ ሃብቶቹን በአግባቡ ለመጠቀምና የተቀናጀ ሕጋዊ መሠረት ለማስያዝ ያስችላል ብለዋል።
በተፋሰሶቹ ላይ ዘላቂነት ያለው የአፈርና ውሀ ጥበቃ ስራ በአግባቡ ከተከናወነ ወደ ሐይቆቹ የሚገባውን ደለል መጠን በከፍተኛ ደረጃ ከመቀነስ ባለፈ ለውኃ ጥራት የሚኖረው ፋይዳ የጎላ መሆኑን አብራርተዋል።
የሀዋሳ ከተማ አስተዳደር አካባቢ፣ደንና አየር ንብረት ለውጥ ቁጥጥር ጽህፈት ቤት ተወካይ አቶ እሼቱ ቦልካ በበኩላቸው፤ የአረንጓዴ ልማት አሻራን ለማሳካት እንደ አስተዳደር ከ2 ሚሊዮን በላይ ችግኝ በላይ ተዘጋጅቶ በተለያዩ አካባቢዎች እየተከከሉ መሆናቸውን ገልጸዋል።
በተከላው ላይ የመንግሥት ሰራተኞች፣አርሶ አደሮች፣የሴቶችና የወጣቶች አደረጃ ጀቶችን በስፋት በማሳተፍ በተያዘው ክረምት ተክሎ ለማጠናቀቅ መታቀዱን አመልክተዋል።
ሀዋሳ ሕይቅን ከደለል ለመታደግ የችገኝ ተከላ ስራው ወሳኝነት እንዳለው ጠቅሰው ይህንን መሰረት ያደረገ ስራ በተፋሰሱ ዙሪያ በስፋት እየተከናወነ እንደሚገኝ አስረድተዋል።
ባለፈው ዓመት በከተማዋና አካባቢዋ 1 ነጥብ 6 ሚሊዮን ችግኝ መተከሉን አስታውሰው በተካሄደው ቆጠራም 83 ነጥብ 4 በመቶ የፅድቀት መጠን መመዝገቡን አመልክተዋል።
በችግኝ ተከላው ላይ ከተሳተፉት መካከል የስምጥ ሸለቆ ሐይቆች ተፋሰስ ልማት ጽህፈት ቤት የአካባቢ ባለሙያ አቶ ወንድሙ ቦጤሼ በሰጡት አስተያየት፤ ባለፉት ሶስት ዓመታት ለችግኝ ተከላ በተሰጠው ትኩረት እንደ ሀገር ውጤታማ በመሆኑ ይህ ተጠናክሮ እንዲቀጥል የተከሉትን ችግኝ እንደሚከባከቡ ተናግረዋል።
የሀዋሳ ከተማ አስተዳደር አካባቢ፣ደንና አየር ንብረት ለውጥ ቁጥጥር ጽህፈት ቤት የብዝሃህይወት ጥበቃና ልማት አስተባባሪ ወይዘሮ ራሄል ሲሳይ በበኩላቸው፤ ከፍተኛ ወጪና ጉልበት ፈሶባቸው የተተከሉ ችግኞች እንክባከባለን ብለዋል።
ከሀዋሳ አውሮፕላን ማረፊያ ዙሪያ ነዋሪዎች መካከል አርሶ አደር አየለ ከበደ በበኩላቸው፤ በሀዋሳ ሐይቅ ዙሪያ የሚተኩሉ ችግኞች በቤት እንስሳት ጉዳት እንዳይደርስባቸው ከለላና ጥበቃ እንደሚያደርጉ ተናግረዋል።