ቀጥታ፡

የቤተክርስቲያኗ አባቶች ወደአንድነት መምጣት በአገር ውስጥና በውጭ ያሉ ኢትዮጵያውያን ትስስር ያጠናክራል - ምዕመናን

አዲስ አበባ ሐምሌ 29/2010 የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን አባቶች በሁለት ሲኖዶስ መከፋፈላቸው አብቅቶ በእርቀ ሰላም ወደአንድነት መምጣታቸው በአገር ውስጥና በውጭ ያሉ ኢትዮጵያውያንን ትስስር እንደሚያጠናክር የቤተክርስቲያኗ ምዕመናን ገልጸዋል። የቤተክርስቲያኗ አንድነት ለኢትዮጵያ ህዝቦች ሰላም፣ መተሳሰብና በጎ የኢትዮጵያዊ ባህል መጠናከር የራሱ ትልቅ ሚና እንደሚኖረውም ተናግረዋል። አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ ምዕመናን እንደገለጹት፤ ሲኖዶሱ ተከፋፍሎ በነበረባቸው አመታት የቤተክርስቲያኗ አገልጋዮች በአገር ውስጥና በውጭ መስጠት የሚገባቸውን አገልግሎት አጠናክረው መስጠት አልቻሉም ነበር። በአባቶች ዘንድ የተፈጠረው መከፋፈል ምዕመናኑ በአንድ ሃይማኖት ውስጥ ሁለት ፓትሪያርኮችን እንዲከተልና በመካከላቸው ክፍተትን የፈጠረ እንደነበር ገልፀው አሁን ግን በውጭ የሚኖረውና በአገር ውስጥ ያለው ተከታይ በአንድ ልብ፣ በአንድ ሲኖዶስ የሚመራበት ጊዜ መምጣቱን አንድነቱን እንደሚያጠናክረው ተናግረዋል። ይህም መንፈሳዊ፣ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ትስስራቸውን የበለጠ እንደሚያጠናክር እምነታቸውን ገልጸዋል። ከዚህ በተጨማሪም ቤተ ክርስቲያኗ ከምትሰጠው መንፈሳዊ አገልግሎት ውጭ  እርቀ ሰላምን በማምጣት፣ ሰላምን፣ አንድነትን በማስተማርና ተያያዥ ኢትዮጵያዊ በጎነትን በማጎልበት ረገድ ትልቅ ሚና ያላት በመሆኗ አንድ መሆናቸው ይህንኑ ያጠናክራል ብለዋል። አቶ ጌታ መሳይ ብዙነህ ኢትዮጵያዊያን ዜጎቻችን በየአለማቱ ተበታትነው በሰሜን አሜሪካ የሚኖሩትን ከአንዱ ሲኖዶስ ወደ ሌለኛው ስነዶስ ማገልገል የማይቻል እንደ ነበረ ገልጸው ቤተክርስትያን አንድ በመሆኗ የመለያየት ችግር እንዲቀፈር ያደርጋል ብለዋል፡፡ ወይዘሮ አዜብ አክሊሉ እንደተናገሩት ሁለቱ ሲኖዶሶች የተለያዬ አስተሳሰብ ላይ ሆነው ተለያይተው መቆየታቸው እጅግ በጣም የሚያሳዝን ሲሆን አሁን ቅዱስ ስነዶሱ አንድ ሆነው ምዕመናንን ለመምራት በመምጣታቸው እጅግ በጣምና ብዙ ትርጉም ያለው ነው ብለዋል፡፡  ወይዘሮ መንበረ ሚካኤል እንደተናገሩት “ይህ አንድነት አንድ ስንሆን አንድ ቃል ነው የሚሰማው፤ አንድ ነገር ነው የምትከተለው፤ ጥላቻ በነበረ ሰአት እዚህ ጋር ምን ተባለ እንደ ኦርቶዶክስ ግራ ያገባል፤ ኢኮኖሚካሊም ስታሰብ አይደለም ለቤተክርስቲያናችን  ለኦርቶዶክስ ለኢትዮጵያ ህዝብ ራሱ ትልቅ መሰረት ነው፤ ጠቅላይ ሚኒስትሩም ከዚህ በመጀመራቸው በጣም ደስ ብሎኛል” ብለዋል፡፡ ከዚህ በፊት በነበረው ችግር በቤተ-ክርስቲያኗም አለመግባባት ተፈጥሮ  ደስታን ያራቀ  ነበር፤ አሁን ግን በርግጠኝነት ያ ሁሉ ነገር ተቀርፎ ወደ ጥሩ መንገድ እየሄድን ነው ያሉት ደግሞ አቶ ዮሐንስ ዘርዓይ ናቸው፡፡ የቤተክርስቲያኗ አባቶች ዘንድ ተፈጥሮ የነበረው መከፋፈል ከሁለት አስርት ዓመታት በላይ አስቆጥሮ በአሁኑ ወቅት እርቀ ሰላም ወርዶ በውጭ ይገኝ የነበረው ሲኖዶስ ወደአገር በመግባት አንድነት መፈጠሩ ይታወቃል። የሲኖዶሶች የዕርቀ ሰላም ማብሰሪያ መርሃ ግብር ትናንት በአዲስ አበባ ሚሊኒየም አዳራሽ ተካሂዷል።        
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም