ቀጥታ፡

ማህበሩ መኖሪያ ቤታቸው ለወደመባቸው ዜጎች 280 ቤቶችን እየገነባ ነው

ጎንደር፤ ሰኔ 19/2013 (ኢዜአ) የኢትዮጵያ ቀይመስቀል ማህበር በማዕከላዊና ምዕራብ ጎንደር ዞኖች በሰው ሰራሽ ችግር ምክንያት መኖሪያ ቤታቸው ለወደመባቸው ዜጎች 280 ቤቶችን እየገነባ መሆኑን ገለጸ፡፡

ማህበሩ ከጭልጋ አካባቢ ተፈናቅለው በጎንደር ከተማ ለሚገኙ 100 አባወራዎች የአልባሳትና የቤት ውስጥ መገልገያ ቁሳቁሶች ድጋፍ ማድረጉም ተመልክቷል።

በኢትዮጵያ ቀይመስቀል ማህበር  የጎንደር ቅርንጫፍ አስተባባሪ አቶ አታለል ታረቀኝ ለኢዜአ እንደተናገሩት ፤ ማህበሩ ቤቶቹን እየገነባ ያለው በዞኖቹ ባለፈው ዓመት ተከስቶ በነበረው ግጭት ቤት ንብረታቸው ለወደመባቸው አባወራና እማወራዎች ነው፡፡

የቤቶቹ ግንባታ የሚካሄደውም ከአሜሪካ ዓለም አቀፍ ተራድኦ ድርጅት / ዩ ኤስ አይ ዲ/ በተገኘ 4 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር ድጋፍ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

የአብዛኛዎቹ ቤቶች ግንባታ 80 በመቶ መጠናቀቁን የጠቀሱት አስተባባሪው፣ በሚቀጥሉት ሁለት ወራት ሙሉ በሙሉ በማጠናቀቅ ለተጎጂዎቹ ለማስረከብ ጥረት እየተደረገ ነው ብለዋል፡፡

ቤቶቹ የመኝታ፣ የምግብ ማብሰያና የግል መጸዳጃ ቤቶችን ያሟሉ መሆናቸውን አመልክተው፤ የአባወራና እማወራዎቹን ፍላጎት መሰረት በማድረግ እየተገነቡ እንደሚገኙ አስረድተዋል።

በሌላ በኩል ማህበሩ በጭልጋ አካባቢ ተፈጥሮ በነበረ ግጭት ተፈናቅለው ወደ ጎንደር ከተማ ለገቡ 100 አባወራዎች ግምታቸው 150 ሺህ ብር የሚያወጡ የብርድ ልብስ፣ መመገቢያና ማብሰያ ቁሶች ትናንት ድጋፍ  አድርጓል፡፡ 

በማህበሩ የአማራ ክልል ቅርንጫፍ ኃላፊ አቶ ሻምበል ዋለ  እንዳሉት፤ ቅርንጫፉ በክልሉ በሰው ሰራሽ ችግር ምክንያት ለተፈናቀሉ ከ70 ሺህ በላይ የህብረተሰብ ክፍሎች ሰብዓዊ ድጋፍ ሰጥቷል፡፡

ባለፉት ዘጠኝ ወራት ከ25 ሚሊዮን ብር በላይ በሚገመት ወጪ በቻግኒና ከሚሴ ጊዜያዊ መጠለያዎች ለሚገኙ ተፈናቃዮች ሰብአዊ ድጋፍ ማቅረቡን አውስተዋል።

ማህበሩ ከዕለት ደራሽ ድጋፍ በተጨማሪ ተፈናቃዮችን በዘላቂነት ለማቋቋም በማዕከላዊና ምዕራብ ጎንደር ዞኖች  120 ቤቶችን ገንብቶ አስረክቧል::

ማህበሩ የአምቡላንስና የተጠፋፉ ቤተሰቦችን በማገናኘት አገልግሎት እንደሚሰጥም ተመልክቷል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም