ቀጥታ፡

በሳዑዲ ዓረቢያ በችግር ላይ የሚገኙ ዜጎችን በ2 ሣምንት ለመመለስ እየተሰራ ነው -- የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር

አዲስ አበባ ሰኔ 19 / 2013 (ኢዜአ) ሳዑዲ ዓረቢያ ውስጥ በችግር ላይ የሚገኙ ዜጎችን በሁለት ሳምንት ውስጥ ወደ አገራቸው ለመመለስ መንግስት እየሰራ መሆኑን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ገለጸ።

ዛሬ ማለዳ 380 የመጀመሪያው ዙር ከሳዑዲ ተመላሾች አዲስ አበባ ገብተዋል።

ተመላሾቹ ቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ሲደርሱ የሠላም ሚኒስትር ዴኤታ ወይዘሮ ፍሬዓለም ሽባባው፣ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ እና ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ሀላፊዎች ተቀብለዋቸዋል።

አምባሳደር ዲና ሙፍቲ በሳውዲ በችግር ላይ የነበሩ ዜጎችን ወደ አገራቸው ለመመለስ ዝግጅት ሲደረግ መቆየቱንና ጉዳዩን የሚያስተባብር ግብረ ሃይል በሳዑዲ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

ወደ አገራቸው ከተመለሱት 380 ዜጎች በተጨማሪ በየቀኑ ሁለት ሺህ ዜጎችን ለመመለስ ውጥን መኖሩንም ተናግረዋል።

በሁለት ሳምንት ጊዜ ውስጥ 40 ሺህ ዜጎችን ለመመለስ እንደሚሰራም አብራርተዋል።  

የሠላም ሚኒስትር ዴኤታዋ ወይዘሮ ፍሬዓለም ሽባባው በበኩላቸው ተመላሾችን ወደ ሥራ ለማሰማራት የሥራ እድል ፈጠራ ኮሚሽንን ጨምሮ ከፍተኛ የሥራ ሃላፊዎችን ያካተተ ቡድን መቋቋሙን ጠቁመዋል።  

በዚሁ መሰረት ቡድኑ ተመላሾች የመጡበትን አካባቢ ከክልሎች ጋር በመነጋገር ከመለየት ጀምሮ የስራ እድል እንዲያገኙ ሁኔታዎች የሚያመቻች መሆኑን አስረድተዋል።  

ተመላሾቹ ራሳቸውን ከመለወጥ ባለፈ ለአገር የሚጠቅም አስተዋጽኦ እንዲያበረክቱ መንግሥት በትኩረት እንደሚሰራም አክለዋል።   

እንደ ሚኒስትር ዴኤታዋ ገለጻ ተመላሾች ወደ ማኅበረሰባቸው እስከሚመለሱ ድረስ ጊዚያዊ ድጋፍ ለማድረግ በብሔራዊ አደጋ ስጋት ኮሚሽን በኩል ዝግጅት ተደርጓል።  

ኮሚሽኑ ጊዚያዊ መጠለያና አስፈላጊ ቁሳቁስ ድጋፍ እንደሚያደርግም አስታውቀዋል።  

ችግሩን ከመሰረቱ ለመግታት ሠላም ሚኒስቴር ከጠቅላይ ዓቃቤ ሕግና ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ጋር እየሰራ መሆኑንም ጠቁመዋል።  

ከተመላሾቹ መካከል ኢብራሂም ሀሚድ ለኢዜአ እንደተናገረው፤ በሪያድ የአንድ ዓመት ቆይታው ዝርፊያ፣ እስርና ድብደባና ስቃይ ገጥሞታል።

"የኢትዮጵያ መንግስት ከሳዑዲ መንግስት ጋር በመነጋገር ለአገሬ ስላበቃኝ ተደስቻለው" ነው ያለው።

"የሰው አገር የሰው ነው ያለው ኢብራሂም" በሕገ ወጥ መንገድ ሄዶ ለችግር ከመዳረግ መጠንቀቅ ይበጃል ሲል ተናግሯል።     

ሌላው ተመላሽ ወጣት ኑሩ መሀመድ ሰኢድም ወደ አገሩ መመለሱ እንዳስደሰተው ገልጾ መንግስት በዚያ የቀሩ ዜጎቹን እንዲመልስ ጠይቋል።  

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር እንደገለጸው በሁለት ሣምንት ውስጥ 40 ሺህ ዜጎች ወደ አገራቸው ይመለሳሉ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም