ቀጥታ፡

የኤሌክትሪክ ኃይል አገልግሎት ባለመመቻቸቱ ወደ ስራ መግባት እንዳልቻሉ የእንጅባራ ወጣቶች ተናገሩ

ባህር ዳር ሀምሌ 29/2010 የኤሌክትሪክ ኃይል አገልግሎት ተደራሽ ባለመሆኑ ምክንያት ወደ ስራ መግባት እንዳልቻሉ በእንጅባራ ከተማ  በማህበር የተደራጁ ወጣቶች ገለጹ። በላይና ጓደኞቹ የብሎኬት ማምረቻ ሽርክና ማህበር ፀሐፊ ወጣት ብርሃኑ ጥላሁን ለኢዜአ እንዳለው መንግስት ከመደበው ተዘዋዋሪ የብድር  ገንዘብ 270 ሺህ ብር ከወሰዱ አንድ ዓመት  ሆኗቸዋል። በብድር ከወሰዱት ገንዘብ 150 ሺህ ብር ወጪ በማድረግ የብሎኬት ማምረቻ ማሽን፣ ጣውላና ሌሎች የስራ ማስጀመሪያ ቁሳቁሶችን አሟልተዋል። "ይሁንና ለማምረቻ የተሰጠን ሼድ ኤሌክትሪክ የተዘረጋለት ባለመሆኑ ወደ ስራ መግባት አልቻልንም"ብሏል ። የብድር መመለሻ የእፎይታ ጊዜያቸው  በማለፉ ከተበደሩት ገንዘብ ውስጥ 18 ሺህ ብር ለመመለስ መገደዳቸውን የገለፀው ወጣት ብርሃኑ" ስራውን ሳንጀምር ባክነን እንቀራለን የሚል ስጋት አሳድሮብናል"ብሏል። "የመብራት ችግር ስራችንን በአግባቡ ሰርተን ብድራችንን በሰዓቱ እንዳንመልስ ፈተና ሆኖብናል" ያለው ደግሞ  ከጓደኞቹ ጋር በብረታ ብረት ስራ ሽርክና ማህበር የተደራጀው ወጣት መልካም ቀን ወርቅነህ ነው፡፡ ሌላው የብሎኬት ማምርቻ ሽርክና ማህበር ፀሐፊ ወጣት ቦጋለ መብራቱ በበኩሉ የኤሌክትሪክ አገልግሎት ባለማግኘታቸው በብድር የወሰዱትን  ገንዘብ  ሳይሰሩበት ከአንድ ዓመት በላይ እንደሆናቸው ተናግሯል። "በተሰጠን የመስሪያ ቦታ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ባለመሟላቱ ወደ ስራ ሳንገባ ቀርተናል"  ያለው ወጣት ቦጋለ  በብድር ከወሰዱት  ገንዘብ ላይ 50 ሺህ ብር እንዲመልሱ መደረጉ የስነ ልቦና ጫና እንዳሳደረባቸው ገልጸዋል። መንግስት አፋጣኝ መፍትሄ እንዲፈልግላቸው ወጣቶቹ ጠይቀዋል። የእንጅባራ ከተማ አስተዳደር ቴክኒክና ሙያ ኢንተርፕራይዞች ጽህፈት ቤት የኢንተርፕራይዞች የስራ ዕድል ፈጠራ ቡድን መሪ አቶ አማኑ ደሳለኝ ስለጉዳዩ ተጠይቀው በሰጡት ምላሽ በ2010 በጀት ዓመት ለ3 ሺህ 185 ወጣቶች የስራ ዕድል መፈጠሩን ገልጸዋል። ለወጣቶቹ ከ6 ሚሊዮን ብር በላይ ተዘዋዋሪ ብድርና በ1 ሚሊዮን 300ሺህ  ብር የተሰሩ ሼዶች ቢሰጧቸውም  በኤሌክትሪክ ችግር ምክንያት ወደ ስራ መግባት እንዳልቻሉ አረጋግጠዋል። በከተማ አስተዳደሩ የከተማ ልማት ቤቶች ኮንስትራክሽን አገልግሎት ጽህፈት ቤት  በኩል በሼዶቹ የኤሌክትሪክ ቆጣሪ ለማስገባት የተጠየቀው 141 ሺህ ብር ለእንጅባራ  አሌክትሪክ አገልግሎት ክፍያ ቢፈፀምም አግልግሎቱ እንዳልተመቻቸም ጠቁመዋል። በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት የእንጅባራ ዲስትሪክት የደንበኞች አገልግሎት ኃላፊ አቶ አየነው ካሳሁን  የከተማ አስተዳደሩ ሼዶችን ሲገነባ ከዲስትሪክቱ ጋር አለመነጋገሩ ለችግሩ ምክንያት መሆኑን ገልጸዋል። ሼዶቹ የተገነቡበት አካባቢ የኤሌክትሪክ መስመር በቀላሉ ለመዘርጋት አዳጋች መሆኑን የገለፁት ኃላፊው በመጪው ወር የመስመር ዝርጋታውን ለማካሄድና ለ20 ሼዶች የሚያገለግሉ 10 ቆጣሪዎችን ለመትከል አቅጣጫ መያዙን አስታውቀዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም