የጅቡቲ እና ድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲዎች ተባብረው በጋራ ለመስራት ተስማሙ - ኢዜአ አማርኛ
የጅቡቲ እና ድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲዎች ተባብረው በጋራ ለመስራት ተስማሙ
ድሬዳዋ፤ ሰኔ 18/2013 (ኢዜአ) የጅቡቲ እና ድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲዎች ልምድ በመለዋወጥ ተባብረው በጋራ ለመስራት ተስማሙ።
የጅቡቲ ዩኒቨርሲቲ ከፍተኛ አመራሮች ዛሬ በድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ ተገኝተው የሥራ ጉብኝትና የጋራ ውይይት አድርገዋል፡፡
በዚህ ወቅት ሁለቱ ዩኒቨርሲቲዎች ልምድ በመለዋወጥ በሣይንስና በቴክኖሎጂው ዘርፍ ጥራቱን የጠበቀ ትምህርት በመስጠት ለሀገራቱ ብሎም ለሌላው አለም የሚተርፍ ባለሙያዎች ለማፍራት ተባብረው ለመስራት ተስማምተዋል፡፡
በተጨማሪም በጥናትና ምርምር ዘርፎች የተቀናጀ ስራ ለማከናወን መግባባት ላይ ደርሰዋል፡፡
ስምምነቱ የተደረገው ሁለቱ ዩኒቨርሲቲዎች ባለፈው የካቲት ወር በጋራ ለመስራት የተፈራረሙትን የመግባቢያ ሰነድ ተከትሎ ነው።
በጅቡቲ ዩኒቨርሲቲ የቀጣናዊ ትብብር ሥራ አስኪያጅ ዶክተር ሙሳ ኬር ሱበግሌ በወቅቱ እንዳሉት፤ ያካሄዱት ጉብኝትና ውይይት አስደሳችና ለቀጣይ ሥራ መደላደል የፈጠረ ነው፡፡
በጋራ መግባቢያው መሠረት በአፍሪካ ቀንድ ያሉ ዩኒቨርሲቲዎች ጋርም ተመሣሣይ ሥራ ይሰራል ብለዋል፡፡
"ጅቡቲ ያላትን ተሞክሮዎችና ሃብቶች እዚህ ላለው ማህበረሰብ እንዲጠቅም ይደረጋል፤ ኢትዮጵያ ያለው ዕውቀት ፣ሃብትና ልምድ ጅቡቲን እንዲጠቅም በጋራ መሰራት መጀመራቸውን አስታወቀዋል፡፡
ይህ የተቀናጀ የዩኒቨርሲቲዎች ግንኙነት ዘመን የተሻገረውን የሁለቱን ሀገራት በጋራ የመልማትና የመበልጸግ ትብብር ይበልጥ ስኬታማ እንዲሆን እንደሚያግዝ ገልጸዋል፡፡
የድሬደዋ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶክተር ኡባህ አደም በበኩላቸው፤ ከጅቡቲ ዩኒቨርሲቲ ጋር በትብብር ለመስራት የተፈረመው የጋራ መግባቢያ ዛሬ በተግባር ዕውን መሆኑን ጀምሯል ብለዋል፡፡
በተለይም ጅቡቲ የአፍሪካ የትራንስፖርትና የሎጂስቲክስ የልዕቀት ማዕከል መኖሩ ለመምህራን የአቅም ግንባታ ለማግኘት ትልቅ ዕድል እንደሚፈጥር ተናግረዋል፡፡
ከሰሞኑ በሲቪልና ኤሌክትሪክ የትምህርት መስኮች የሁለተኛ ዲግሪ የትምህርት ዕድል ለማግኘት መምህራን ወደ ጅቡቲ እንደሚጓዙ ጠቁመዋል፡፡
በጥናትና ምርምር መስክም ከፍተኛ ሥራ መስራት ይጀመራል፤ ስምምነቱ በሁለቱ ዩኒቨርሲቲዎች ያሉ ሃብቶችን በጋራ በመጠቀም የጋራና ቀጠናዊ ዕድገትን ለማምጣት ያስችላል ብለዋል፡፡
እንደ ዶክተር ኡባህ ገለጻ ፤ ከጅቡቲ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር መስራቱ የድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ በቀጠናው ላይ ተቀባይነቱንና ተመራጭነቱን ለማረጋገጥ መደላደል ይፈጥርለታል፡፡
ትብብሩ ከሁሉም በላይ የኢትዮጵያ ጅቡቲ የህዝብ ለህዝብ፣ የማህበራዊና የምጣኔ ሃብት ሁለንተናዊ ግንኙነት እንዲጠናከር ያግዛል ብለዋል፡፡
ወደ ተግባር የተለወጠው በጋራ የመስራት ስምምነት ጥራቱን የጠበቀ ትምህርት በመስጠት ሌላው አለም ጭምር የሚተርፍ ባለሙያዎችን ለማፍራት ወሳኝ ቀጠናው ትብብር እንደሚሆን የገለጹት ደግሞ በድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ የሣይንስና ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ሣይንቲፊክ ዳይሬክተር ዶክተር መርሃዊት ብርሃኑ ናቸው።