ቀጥታ፡

በሕዝብ ድምፅ ተመርጦ መንግስት የሚመሰርተው ፓርቲ የዜጎችን ችግሮች መፍታት ይጠበቅበታል - አስተያየት ሰጪዎች

አዲስ አበባ ሰኔ 18 ቀን 2013 (ኢዜአ) በሕዝቡ አብላጫ ድምጽ አግኝቶ መንግስት የሚመሰርተው ፓርቲ ስር የሰደዱ የዜጎች ችግር ላይ ትኩረት አድርጎ እንዲሰራ አስተያየታቸውን የሰጡ የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ጠየቁ።

6ተኛው አገራዊ ምርጫ በሠላም ተጠናቋል፤ መራጮችን ጨምሮ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ ታዛቢዎችና ሂደቱን የተከታተሉ አካላት ምርጫው ዴሞክራሲያዊ፣ ፍትሃዊና ነፃ እንደነበረ ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት በመጪው መስከረም በሕዝብ አብላጫ ድምጽ አግኝቶ መንግስት የሚመሰርተው ፓርቲ ምን ይጠበቅበታል ሲል የመዲናዋን ነዋሪዎች አነጋግሯል።

አስተያየት ስጪዎቹም አዲስ የሚመሰረተው መንግስት ዜጎች ያለገደብ ተንቀሳቅሰው ሰርተው የሚያተርፉበትና ህይወታቸውን የሚቀይሩበት፤ለሁሉ የምትመች አገር ለመፍጠር መስራት እንዳለበት አመልክተዋል።

በተለይም ስር የሰደዱ ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ችግሮችን ነቅሶ በማውጣት መፍትሄ ለማምጣት በትኩረት ሊሰራ እንደሚገባ ነው የተናገሩት።

በአገሪቷ ሠላም እንዲሰፍን፣ ወጣቶች ስራ እንዲያገኙ፣ የኖሮ ውድነቱ እንዲረግብ እንዲሁም የአካል ጉዳተኞችን ታሳቢ ያደረገ ስራ እንዲሰራ እንደሚሹም ገልጸዋል።

ከአስተያየት ሰጪዎች መካከል አቶ ፋንቱ ወርቁ እንደሚሉት በምርጫው አሸንፎ ወደ ስልጣን የሚመጣው ፓርቲ የኢትዮጵያ ህዝብን በእኩል አይን ሊያገለግል ይገባል፡፡  

ወጣቶች ላይ ትኩረት በማድረግ መስራት ቢችል መልካም ነው ያሉት ደግሞ ወይዘሮ አለሚቱ ጥላሁን ናቸው፡፡ወ/ሮ አለሚቱ ጨምረውም መንግስት በገበያው ላይ ገብቶ የኑሮ ውድነትን ማረጋጋት አስተያየጣቸው ሰጥተዋል፡፡

በመጪው መስከረም መንግስት የሚመሰርተው ፓርቲ ለሕዝብ ጥያቄዎች ምላሽ ሊሰጥ እንደሚገባም ነዋሪዎቹ አመልክተዋል።

መንግስት ሆኖ የሚመጣው ፓርቲ ሕዝብ የሚያነሳቸውን የልማት፣ የስራ አጥነትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች መመለስ ይኖርበታል ብለዋል።

በቀጣይ መንግስት ከሚመሰርተው ፓርቲ ብዙ ለውጦች እንደሚጠብቅ ገልጾ አገራዊ አንድነትና ወንድማማችነት ላይ መስራት ይጠበቅበታል ሲሉም ተናግረዋል።

አስተያየት ሰጪዎቹ የሚመሰረተው መንግስት በኑሮ ውድነትና በአገራዊ አንድነት ላይ የሚስተዋሉ ችግሮችን በመለየት መስራት አለበት ሲሉ ጠቁመዋል።

አዲስ የሚመጣው መንግስት አገሪቷ ካሳለፈቻቸው ዓመታት የነበሩ ጥያቄዎችን ምላሽ መስጠት እንደሚገባው አቶ ሰይፉ ገብረማርያም ገልፀዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም