ቀጥታ፡

የበይነ መረብ መገናኛ ብዙሃንን ለብሔራዊ ጥቅም ማስጠበቂያነት መጠቀም ይገባል - የሚዲያና ኮሙኒኬሽን ባለሙያዎች

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 18 ቀን 2013 ዓ.ም (ኢዜአ) የበይነ መረብ መገናኛ ብዙሃንን ሉዓላዊነትና ብሔራዊ ጥቅምን ለማስጠበቅ መጠቀም እንደሚገባ ኢዜአ ያነጋገራቸው የሚዲያና ኮሙኒኬሽን ባለሙያዎች ገለጹ።

በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ላይ ትኩረት አድርገው የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም ለማስጠበቅ የሚሰሩት ባለሙያዎቹ እንደገለጹት፤ የበይነ መረብ መገናኛ ብዙሃንን የአገር ሉአላዊነትና ብሔራዊ ጥቅምን ለማስከበር ማዋል ይገባል።

ዜጎች ቴክኖሎጂ የፈጠረላቸውን እድል ተጠቅመው በኢትዮጵያ ላይ የሚደረጉ ጫናዎችና የተዛቡ መረጃዎችን መመከት እንዳለባቸውም አመልክተዋል።

ኢትዮጵያዊያን በሕዳሴ ግድቡ ዙሪያ ዓለም አቀፍ ተጽዕኖ ለመፍጠር የጀመሩት እንቅስቃሴ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበትም አንስተዋል።

"የዲጂታል ሚዲያው አብዮት በፍጥነት እየተለዋወጠ ነው” የሚለው ጋዜጠኛ ስለአባት ማናዬ፤ በበይነ መረብ መገናኛ ብዙሃን አማካኝነት የአገሪቱን ብሔራዊ ጥቅም ለማስጠበቅ በበቂ መጠን እንዳልተሰራ ገልጿል።

“በተወሰነ ደረጃ በበጎ ፈቃደኞች፣ በጋዜጠኞች እንዲሁም መደበኛ መገናኛ ብዙሃንም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የተወሰነ ተስፋ ሰጪ እንቅስቃሴ አላቸው” በማለት ተናግሯል።

በማህበራዊ ሚዲያ የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም ለማስጠበቅ ጥረት እያደረገ የሚገኘው ኪራም ታደሰ በበኩሉ የአገርን ጥቅም፣ የህዝብን ፍላጎት በበይነ መረብ መገናኛ ብዙሃን ማስተዋወቅ እንደሚገባ አስገንዝቧል።

"የአገራዊ ጥቅምን፣ ፍላጎትን የሕዝቦችን ፍላጎት በዲጂታል ፕላትፎርሞች በመጠቀም ማስተዋወቅ የሕዝቦችን ፍላጎት መነሻና መድረሻ ማስተዋወቅ መቻል ነው” ብሏል።

ወቅቱ ይህንን ለማድረግ አመቺ መሆኑን ገልጾ፤ ከህዳሴ ግድቡ ጋር በተያያዘ በዚህ ረገድ እየተሰራበት እንደሚገኝ አመልክቷል።

“ዲጂታል ዲፕሎማሲ ሁሉም በግል ተነሳሽነት እንቅስቃሴ ያደርጋል” ያለው ኪራም ታደሰ፤ ይህንን ስራ አለም ዓቀፍም ሆነ ሌሎች መደበኛ መገናኛ ብዙሃን የሚሰሩት ስራ እንደሆነም ጠቅሷል።

ሌላው ጋዜጠኛ ሰላም ሙሉጌታ በበኩሉ "በማኅበራዊ ሚዲያ ትልቅ ስራ እየተሰራ ነው” ብሏል።

“ትልቁ አገራዊ አጀንዳችን በሆነው በአባይ ጉዳይ ላይ ማኅበረሰብን በማንቃት ብሎም ጥቅሞቻችንን የሚነኩ የባላንጣ አገራት ፕሮፓጋንዳዎችን፣ የሃሰት መረጃዎችን በመከላከል በተጨማሪም የራሳችንን እውነተኛ መረጃ፣ የእኛን መገለጫ፣ የእኛን ጥሬ ሃቆች ለዓለም ለማድረስ እየተጠቀምንበት ነው” በማለት የማህበራዊ ሚዲያ እየሰጠ ስላለው ጥቅም ተናግሯል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም