ቀጥታ፡

አሸናፊ የሚሆነው ፓርቲ የኑሮ ውድነትን ማስተካከል የመጀመሪያ ተግባሩ መሆን አለበት- አስተያየት ሰጪዎች

ባህር ዳር፤ ሰኔ 17/2013 (ኢዜአ) በስድስተኛው ጠቅላላ ምርጫ አሸናፊ የሚሆነው የፖለቲካ ፓርቲ እየተባባሰ የመጣውን የኑሮ ውድነትን ማስተካከል የመጀመሪያ ተግባሩ መሆን እንዳለበት በደብረ ማርቆስ ከተማ አስተያየታቸውን የሰጡ ነዋሪዎች ተናገሩ።

የዘንድሮ ምርጫው በሰላምና ፍትሃዊ ሆኖ መጠናቀቁ የሚስተዋሉ ችግሮችን ደረጃ በደረጃ ለመፍታት አቅም እንደሚፈጥርም አስተያየት ሰጪዎቹ ገልጸዋል።

ከነዋሪዎቹ መካከል ወይዘሮ አለምፀሐይ አስራት እንዳሉት፤ አሁን ላይ ከሸቀጣ ሸቀጥ እስከ ምግብ እህል ያለው የዋጋ ንረት እየተባባሰ መጥቷል።

"እኔ የመንግስት ሰራተኛ በመሆኔ በወር በማገኘው ደመወዜ እተዳደራለሁ" ያሉት ወይዘሮ አለምፀሐይ በአካባቢያቸው አቅመ ደካሞችና ገቢያቸው ዝቅተኛ የሆነ የህብረተሰብ ክፍሎች ተቸግረው እንዳሉ አስረድተዋል።

በምርጫው አሸናፊ የሚሆነው ፓርቲ መንግስት ሲመሰርት የመጀመሪያ ስራው በምግብና ምግብ ነክ ቁሳቁሶች ላይ የተከሰተውን የዋጋ ንረትን ማስተካከል  የመጀመሪያ ተግባሩ መሆን እንዳለበት ተናግረዋል።

በከተማዋ  የቀበሌ ሰባት ነዋሪ አቶ ያለው ቢተው በበኩላቸው፤ አሁን ላይ የምግብና ሸቀጦች ዋጋ መናር ችግር አሳሳቢ መሆኑን ገልጸዋል።

ጤፍ በስፋት በሚመረትበት ጎጃም ምድር  አንድ ኩንታል ጤፍ 4ሺህ 800 ብር መሸጡ የችግሩን አሳሰቢነት እንደሚያሳይ ጠቅሰዋል።

በአካባቢያቸው አሁን ላይ የኑሮ ውድነት አስቸጋሪ በመሆኑ አሸናፊው ፓርቲ ይህን ለማስተካከል  ጠንከራ እርምጃ በመውሰድ ህዝቡ እፎይታ የሚያገኝበትን ሁኔታ ማመቻቸት እንዳለበት አመልክተዋል።

“በዚህ ምርጫ አሸናፊ የሆነው ፓርቲ የመጀመሪያው ተግባር መሆን ያለበት በህብረተሰቡ ውስጥ ያሉ ችግሮችን ነቅሶ መለየት ነው” ያሉት ደግሞ ሌላው የከተማዋ ነዋሪ አቶ አበረ መንግስት ናቸው።

ችግሮችን በጥናት ከለየ በኋላ  በአጭር፣ መካከለኛና ረጅም ጊዜ ለመፍታት የሚያስችል መርሃ ግብር በመንደፍ አፋጣኝ ምላሽ መስጠት እንዳለበት ተናግረዋል።

በተጨማሪም አዳዲስ ለውጦችን ለማምጣትና የተጀመሩትን ለማስቀጠል በትኩረት በመስራት ሀገሪቱ  ከገጠማት ችግር የሚታደግ መንግስት መሆን አለበት ብለዋል።

በሀገሪቱ አሁን ላይ የሚስተዋሉ ችግሮችን ለመፍታትም ስድስተኛው ጠቅላላ  ምርጫ በሰላም ማጠናቀቅ መቻሉ አቅምና ጉልበት ሆኖ ሊያግዝ እንደሚችል አስተያየት ሰጪዎቹ ገልጸዋል።

በሀገሪቱ ስድስተኛው ዙር ጠቅላላ ምርጫ  ሰኔ 14/2013ዓ.ም መካሄዱና ወደ ጷጉሜን 1/2013ዓ.ም. ተላልፎ የሚካሄድባቸው አካባቢዎች እንዳሉም የኢትዮጵያ ብሔራዊ  ምርጫ ቦርድ ቀደም ብሎ ማስታወቁ በወቅቱ ተገልጿል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም