ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ ከፖለቲካ ፓርቲዎች የሚቀርበውን አቤቱታ እየተቀበለ መሆኑን አስታወቀ

አዲስ አበባ፤ ሰኔ 17/2013 (ኢዜአ) የኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ ከተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲዎች የሚቀርቡለትን አቤቱታዎች እየተቀበለ መሆኑን አስታወቀ።

ምርጫ በተከናወነባቸው ቦታዎች በአብዛኛው የምርጫ ጣቢያዎች ውጤት ተጠናቆ ወደ ምርጫ ክልሎች እየገባ መሆኑም ተገልጿል።

የኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ብርቱካን ሚደቅሳ፤ ከምርጫው መጠናቀቅ በኋላ ቦርዱ እያከናወነ ያለውን እንቅስቃሴ በተመለከተ መግለጫ ሰጥተዋል።

በመግለጫቸውም ቦርዱ ባቋቋመው ዴስክ በኩል የፖለቲካ ፓርቲዎች ያጋጠማቸውን ችግርና ቅሬታ በመቀበል ላይ ይገኛል ብለዋል።

በተለይም በአማራና ደቡብ ክልሎች ታዛቢዎች ወደ ምርጫ ጣቢያ እንዳይገቡ ተከልክሏል የሚሉ ቅሬታዎችን ጨምሮ ሌሎች አጋጠሙ የሚሏቸውን ችግሮች ቦርዱ መቀበሉን ጠቅሰዋል።

ከቀረቡት አቤቱታዎች መካከል አንዳንዶቹ በቦርድ ደረጃ ሳይሆን ምርጫ ጣቢያዎች ላይ የሚታዩ መሆናቸውን ገልጸው፤ አንዳንዶቹም በዕለቱ መፈታታቸውንም አብራርተዋል።

አንዳንዶቹ የምናያቸው ጉዳዮች የምርጫ ውጤቱን የማይቀይሩ ናቸው ያሉት ሰብሳቢዋ፤ ሆኖም ቦርዱ የተቀበላቸውና የሚያያቸው መሆኑን ጠቁመዋል።

ከአንዳንዶች ደግሞ ዝርዝር ማብራሪያ የሚጎድላቸው አቤቱታዎች መቅረባቸውን ገልጸዋል።በአብዛኛው የምርጫ ጣቢያዎች ውጤት ተጠናቆ ወደ ምርጫ ክልሎች እየገባ መሆኑም ተገልጿል።

በአማራ ክልል ከድል ይብዛ ምርጫ ክልል 11 ምርጫ ጣቢያዎች በአፋር ዳሎል ምርጫ ክልልና በሲዳማ ክልል ከአርቤጉና ምርጫ ክልል በስተቀር ሁሉም ውጤቶች ተጠቃለው ወደ ምርጫ ክልል እየገቡ መሆናቸውን አስታውቀዋል።

እነዚህ የዘገዩትም አንዳንዶቹ ከትራንስፖርት አቅርቦት ጋር የተያያዘ ሲሆን ሲዳማ ክልል ዘግይቶ ምርጫ ከመካሄዱ ጋር የታያያዘ መሆኑን ገልጸዋል።

አጠቃላይ ምርጫውን በተመለከተ ከ40 ሺህ በላይ የአገር ውስጥ ታዛቢዎችን ጨምር የአፍረካ ህብረትና የኢስት አፍሪካ ስታንድ ባይ ኦብዘርቨር የታዛቢዎች ቡድን መሰማራቱን ገልፀዋል።

ታዛቢዎች ባቀረቡት የመጀመሪያ የትዝብት ሪፖርት መሰረት አብዛኞቹ እንደ ጥሩ ግብዓት የሚወሰዱ ናቸዉ ብለዋል።

በተለይ የአገር ውስጥ ታዛቢዎች ከምርጫው እለት ጀምሮ በሚሰጡት አስተያየትና ጥቆማ መሰረት "በዕለቱ የእርምት እርምጃ እንድንወስድ አግዘውናል" ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም