ቀጥታ፡

ምርጫው ለሌሎች አገራት ምሣሌ የሚሆን ነው - አምባሳደር ዲና ሙፍቲ

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 17/2013 (ኢዜአ) 6ኛው አገራዊ ምርጫ ለሌሎች አገራት ምሣሌ በሚሆን መልኩ መጠናቀቁን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ ገለጹ።

አምባሳደር ዲና ዛሬ በሰጡት ሣምንታዊ መግለጫቸው ኢትዮጵያ 6ኛውን ጠቅላላ ምርጫ በሠላምና ሂደቱን በጠበቀ መልኩ ማከናወኗን ለዓለም አሳይታለች ብለዋል።

አንዳንድ አካላት ምርጫውን ተከትሎ በኢትዮጵያ ግጭቶች ይኖራሉ የሚል ትንበያና ምኞት ቢኖራቸውም ሕዝቡ የሚያኮራ ሠላማዊ ምርጫ ማካሄዱን ተናግረዋል።

በአገሪቷ የተለያዩ አካባቢዎች መራጩ ሕዝብ ድምጽ መስጠት ከተጀመረበት ከማለዳው 12 ሠዓት ጀምሮ በትዕግስት ድምፁን መስጠቱን ገልጸዋል።   

ያም ብቻ ሳይሆን ምርጫው ሠላማዊ፣ ቅደም ተከተላዊ ሥርዓቱን የተከተለና ተዓማኒ መሆኑ በአፍሪካ ኅብረት ምርጫ ታዛቢ ቡድን መገለጹንም ለአብነት አንስተዋል።

ስለዚህም ምርጫው ለሌሎች የዓለም አገራት ምሣሌ መሆን በሚችል መልኩ መጠናቀቁን ነው ያወሱት።

በሌላ በኩል የአፍሪካ ኅብረት የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን በትግራይ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ለማጣራት በተናጠል የሚያደርገውን ጥረት ኢትዮጵያ ውደቅ አድርጋዋለች ብለዋል።

ይህ አይነቱ አካሄድ የኢትዮጵያ መንግሥት ጉዳዩ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በጋራ የሚያደርገውን የማጣራት ሥራና የትብብር መንፈስ የሚያንኳስስ መሆኑን ተናግረዋል።

ዜጋ ተኮር ዲፕሎማሲን በተመለከተም ባለፈው ሣምንት ብቻ ከሳዑዲ ዓረቢያ፣ ከኬንያና ከሶማሊያ 1 ሺህ 191 ዜጎች ወደ አገራቸው መመለስ እንደተቻለ ጠቅሰዋል።

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በሳዑዲ በችግር ላይ የሚገኙ ዜጎችን በ15 ቀናት ሙሉ በሙሉ ወደ አገራቸው ለመመለስ እየተሰራ መሆኑም ነው ያስረዱት።

ለዚህም ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርን ጨምሮ ከተለያዩ ተቋማት የተውጣጡ ባለሙያዎች የተሳተፉበት አንድ ልዑክ ወደ ሳዑዲ መላኩን አምባሳደር ዲና ገልጸዋል።   

በተጓዳኝም ሱዳን የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ጉዳይ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የጸጥታው ምክር ቤት እንዲካሄድ የጠየቀቸውን ጥያቄ ኢትዮጵያ እንደማትቀበለው ጠቁመዋል።

"ችግሩ የአፍሪካ ነው፤ ውሃው አፍሪካዊ ነው በአፍሪካ መፈታት አለበት" ሲሉ ነው አምባሳደር ዲና የገለጹት።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም