ቀጥታ፡

ጠንካራ የእምነትና የባህል ተቋማት ሳይኖሩ ጠንካራ ኢትዮጵያን ማሰብ እንደማይቻል ፕሬዝዳንት ዶክተር ሙላቱ ተሾመ ገለፁ

አዲስ አበባ ሀምሌ 28/2010 ጠንካራ የእምነትና የባህል ተቋማት ሳይኖሩ ጠንካራ ኢትዮጵያን ማሰብ እንደማይቻል ፕሬዝዳንት ዶክተር ሙላቱ ተሾመ ገለፁ። ዛሬ በሚሊኒየም አዳራሽ በተካሄደው የዕርቅ ማብሰሪያ በተዘጋጀ ስነስረአት ላይ ባደረጉት ንግግር በሁለቱም ሲኖዶሶች የነበረው ችግር መፈታቱ እንዳስደሰታቸው ተናግረዋል። ፕሬዝዳንቱ እንደገለፁት በአገሪቱ ታሪክ ሰላምና ልማት እንዲረጋገጥና ቅርሶች እንዲጠበቁ ቤተ ክርስቲያኒቱ ትልቅ አስተዋፅኦ ስታደርግ ቆይታለች። ከዚህ በተጨማሪ  ቤተክርስቲያኒቱ በስነ ፅሑፍ፣ በጥበብና በስነ ቅርስ ትልቅ አስተዋፅኦ አበርክታለችም ብለዋል። ቤተ ክርስቲያኗ ለአፍሪካውያን የነፃነት ተምሳሌት ሆና ስትቆጠር ቆይታለች ያሉት ፕሬዝዳንቱ አሁንም በአባቶች መካከል የነበረውን ልዩነት በራስ አቅም በመፍታት ኢትዮጵያ ትልቅ አቅም እንዳላት አሳይታለች ነው ያሉት። ፕሬዝዳንቱ ባደረጉት ንግግር የአገሪቱ የእምነት ተቋማት በጋራ በመደጋገፍ ባህል በአገሪቱ ልማት ላይ አወንታዊ አስተዋጽኦ እንዲያደርጉ አሳስበዋል። ከዚህ በተጨማሪ ወጣቱ ትውልድ በሱስና በመጤ ባህል እንዳይጠቃ የእምነት ተቋማት የአስተምህሮ ስራዎችን አንዲሰሩም አሳስበዋል። የቤተክርስቲያኗ የቀድሞ ፓትሪያርክና የወቅቱ ፓትሪታርክ በተካሄደው የዕርቅ ማብሰሪያ ፕሮግራም መልዕክቶችን አስተላልፈዋል። የቤተክርስቲያኗ ፓትሪያርክ አቡነ ማቲያስ ባስተላለፉት መልዕክት "ከዛሬ ጀምሮ ልዩነቶች ተፈትተው ሁሉም ዜጋ በአንድነት ይቁም" ብለዋል። አገሪቱን ወደ ነበረችበት የጥንት ገናና ታሪኳ ለመመለስ ሁሉም ዜጋ አሁን በተጀመረው ለውጥ ጥረቱን እንዲቀጥል በማሳሰብ ሁሉም ዜጋ ከዕርስ በርስ ግጭቶች እንዲርቅ አባታዊ ምክር ለግሰዋል። ቤተ ክርስቲያኗም የአገሪቱን አንድነት ለማጠናከር የሚጠበቅባትን ሁሉ ታደርጋለችም ብለዋል። አራተኛው የኢትዮጵያ ፓትሪያርክ አቡነ መርቆሬዎስ በአቡነ ቴዎፍሎስ በኩል ባስተላለፉት መልዕክት ወጣቱ ትውልድ አገሪቱን ወደ ቀድሞ ገናና ክብሯን ለመመለስ እንዲሰራ አሳስበዋል። ትውልዱ ዘረኝነትን በመጠየፍ ዘመን ተሻጋሪ የሆነውን የመተማመንና መከባበርን ባህል እንዲያጎለብት ቤተ ክርስቲያን እንደምትሰብክ አረጋግጠዋል። ግጭቶችን በሰለጠነ መንገድ በመፍታት ሰላምና አንድነትን የማረጋገጥ ስራ እንዲሰራ ያሳሰቡት አቡነ ቴዎፍሎድ ለተደረገላቸው አቀባበል ለአቡነ ማቲያስ፣ለጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይና ለመላው ኢትዮጵያዊያን ምስጋና አቅርበዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም