በህደሴ ግድብ የውጭ ጣልቃ ገብነትን ለመግታት ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነትን ማጠናከር ይገባል... ምሁራን - ኢዜአ አማርኛ
በህደሴ ግድብ የውጭ ጣልቃ ገብነትን ለመግታት ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነትን ማጠናከር ይገባል... ምሁራን
ባህር ዳር፤ ሰኔ 17/2013 ( ኢዜአ) -በታላቁ ህዳሴ ግድብ ላይ እየተስተዋለ ያለውን የውጭ ጣልቃ ገብነትን ለመግታት ግንባታውን ከማፋጠን ጎን ለጎን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነትን አጠናክሮ መቀጠል ይገባል ሲሉ ምሁራን አመለከቱ።
የደብረ ማርቆስ ዩኒቨርስቲ የታክ መምህር ዶክተር ይሄይስ አረጉ ለኢዜአ እንደገለጹት የኢትዮጵያን እድገት የማይፈልጉና ከታችኛው የተፋሰስ ሀገራት ጋር በጥቅም የተሳሰሩ የውጭ ሀገራት በህዳሴው ግድብ ላይ እያደረጉ ያለው ጣልቃ ገብነት ተገቢ አይደለም።
ኢትዮጵያ የተፈጥሮ መብቷን ፍትሀዊ በሆነ መንገድ የመጠቀም መብቷን መሰረት በማድረግ አባይን ገድባ ለኤሌክትሪክ ሀይል ማመንጫነት፣ ለመስኖና ለሌሎች ልማቶች ለማዋል ለጀመረችው ተግባር የማንንም ፈቃድ መጠየቅ የማይገባት መሆኑን ተናግረዋል።
"ነገር ግን የኢትዮጵያን ማደግና መበልፀግ የማይፈልጉ የጎረቤትና የአውሮፓ ሃገራት በቀጥታና በተዘዋዋሪ ግድቡ እንዳይሳካ ከባድ ጫና እየፈጠሩ ይገኛሉ" ብለዋል።
በተለይም ሱዳንና ግብፅ ጥምረት ፈጥረው በኢትዮጵያ ላይ እያሳዩ ያለው ተለዋዋጭና በመርህ የማይመራ ዴፕሎማሲ እንቅስቃሴ እራሳቸውን ብቻ የተመለከቱበትና የኢትዮጰያን ጥቅም ሙሉ በሙሉ የሚገፋ መሆኑን አመልክተዋል።
የኢትዮጵያ መንግስት እየተስተዋለ ያለውን ጫና ለማቃለልና ለመግታት የግድቡን ስራ በፍጥነት አጠናቆ ወደ ስራ የማስገባት ጉዳይ ቅድሚያ ሊሰጠው የሚገባ ተግባር መሆኑን ተናግረዋል።
ከዚሁ ጎን ለጎን የዴፕሎማሲ ስራውን ማጠናከር እንደሚገባ የገለፁት ዶክተር ይሄይስ የወቅቱ ቴክኖሎጂ በሚፈቅደው በማንኛውም የመገናኛ አውታር በመጠቀም ከምእራቡም ሆነ ከምስራቁ ሀገራት ጋር ያለንን መልካም ግንኙነት ማጠናከር እንደሚገባ አመልክተዋል።
ኢትዮጵያ የተፈጥሮ ሀብቷን የመጠቀም መብትና ፍትሀዊ የውሀ የአጠቃቀም አለም አቀፍ መርህን መሰረት አድርጋ ግድቡን መገንባቷን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነትን በጠበቀ አግባብ የማስረዳትና የማሳመን ጥረቷን አጠናክራ ልትቀጥል እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
''ጎረቤተ ሃገር ግብፅና ሱዳን ድሮውንም ቢሆን ለኢትዮጰያ እድገትና ብልፅግና ያስባሉ ተብሎ አይጠበቅም'' ያሉት ደግሞ በኮተቤ ሜትሮፖሊታንት ዩኒቨርስቲ የታሪክ መምህር ዶክተር አልማው ክፍሌ ናቸው።
እሳቸው እንዳሉት በኢትዮጵያ ላይ በሰበባስበቡ እየተደረገ ያለው የውጭ ጣልቃ ገብነትም ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊና ፖለቲካዊ ጉዳዮችን ያነገበ እንደሆነ አመልክተዋል።
በአባይ ግድብ ስበብ በኢትዮጵያ ላይ እየተፈጠረ ያለው ጫና ምስራቅ አፍሪካን ብሎም መላው አፍሪካን በመቆጣጠር የእጅ አዙር ቅኝ ግዛት ከማስፋፋት ፍላጎት ጋር የተያያዘ እንደሆነ ጠቁመዋል።
ጣልቃ ገብነቱን ለመቋቋምና ለመግታት እውነታን መናገር የሚችሉና በዲፕሎማሲው ስራ በእውቀትና በክህሎት የተሻለ አቅም ያላቸው ሰዎችን መጠቀም እንደሚገባ አመልክተዋል።
አቅሙ ያላቸው ሰዎችን በመጠቀም ከሀገራት ጋር ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነትን በማጠናከርና በዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙሀን በሚደረግ የፊት ለፊት ውይይት ጫናዎችን ማቃለል እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
ኢትዮጵያ አሁን ላይ እየተደራደረችበት ያለውን የበሰለ ስልትና አቅጣጫ አጠናክሮ መቀጠል እንደሚገባ አስታውቀዋል።
የኢትዮጵያ መንግስት የታላቁን ህዳሴ ግድብ ግንባታ ቀን ከሌት በመስራት ከማፋጠን ጎን ለጎን የዴፕሎማሲ ድርድሩን በላቀ ብልሃት መቀጠል አለበት ምሁራኑ አመልክተዋል።