ቀጥታ፡

አሸባሪው የህወሃት ቡድን የተለያዩ ቦታዎችን እንደተቆጣጠረ አስመስሎ የሚያሰራጨው መረጃ ከእውነት የራቀ ነው... የአገር መከላከያ ሰራዊት

አዲስ አበባ፤ሰኔ 17/2013(ኢዜአ) አሸባሪው የህወሃት ቡድን የተለያዩ ቦታዎችን እንደተቆጣጠረ አስመስሎ የሚያሰራጨው መረጃ ከእውነት የራቀ መሆኑን የአገር መከላከያ ሰራዊት አስታወቀ።

የመከላከያ ሰራዊት ህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር ኮሎኔል ጌትነት አዳነ በወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ ዛሬ መግለጫ ሰጥተዋል።

በመግለጫቸው በኢትዮጵያ የተካሄደውን 6ኛው ሀገራዊ ምርጫ ለማደናቀፍ ከውጭም ከውስጥም የደህንነት ስጋቶች እንደነበሩ አንስተዋል።

በመሆኑንም በመንግስት ትእዛዝ መሰረት በትግራይ ክልል በህግ ማስከበር ዘመቻ ውስጥ የነበሩ የመከላከያ ሰራዊት አባላት በተለያዩ የኢትዮጵያ አከባቢዎች እንዲንቀሳቀሱ ተደርጓል ነው ያሉት።

በዚህም ሰራዊቱ ወደ ማዕከል፣ምስራቅ፣ምዕራብና ደቡብ ባሉ የአገሪቱ ክፍሎች እንዲንቀሳቀስ መደረጉን ነው የገለፁት።

በተጨማሪ በክረምቱ ወራት በትግራይ ያሉ አርሶ አደሮች ሳይረበሹ የእርሻ ስራቸውን እንዲያካሂዱ በሚል ምክንያት ሰራዊቱ ወደ ሌሎች አካባቢዎች እንቅስቃሴ ማድረጉንም በማብራራት፤ በትግራይ የነበረው ቀሪ ሃይል መሰረተ ልማት የመጠበቅና ሌሎች ኃላፊነቶች ላይ ተሰማርቶ መቆየቱን አንስተዋል።

አሸባሪ ቡድኑ ይህን እንደ መልካም አጋጣሚ በመጠቀም በየቤቱ ተደብቆ የነበረውን የቡድኑን ሚሊሻ ድል እንዳደረገ በማስመሰል መጨፍር መጀመሩን ገልጸዋል።

በተጨማሪ መከላከያ ሰራዊቱ ለሌላ ስምሪት የለቀቃቸውን ቦታዎች አሸባሪ ቡድኑ እንዳስለቀቀው አስመስሎ የሀሰት ፕሮፓጋንዳ እያሰራጨ መሆኑንም ተናግረው፤ አሸባሪ ቡድኑ የሀሰት ዘመቻ የምርጫውን በሰላም መጠናቀቅ አጀንዳ ለማስቀየር ያለመ መሆኑንም ኮሎኔል ጌትነት ገልጸዋል።

አሸባሪው ቡድኑ እድሜያቸው ለጦርነት ያልደረሱ ህጻናትን ሀሽሽ በማስጨስና ከኋላ በመሳሪያ በማስፈራራት ለጦርነት እየገፋቸው መሆኑንም ተናግረዋል።

ነገር ግን የመከላከያ ሰራዊት ህጻናትን ላለመጉዳት በጥንቃቄ ግዳጁን እየተወጣ መሆኑን ገልጸዋል።

ቡድኑ ወደ ውጭ የማምለጫ መንገዶቹ ስለተዘጉበትና ከባድ ኪሳራ ስለገጠመው የአሁኑ የሀሰት ዘመቻ አለሁ በማለት የዓለም መንግስታት ከመንግስት ጋር እንዲያደራድሩት በመፈለጉ መሆኑንም አብራርተዋል።

"አሸባሪው ቡድን ገና ከጅምሩ ጦርነቱን ህዝባዊ፣ ቀጠናዊ እናደርገዋለን" ብሎ በመዛት በጎረቤት ሀገር ኤርትራ ሮኬት መተኮሱንም አስታውሰዋል።

በውጊያ ፈርጥጦ የነበረው አሸባሪው ቡድን በሚነዛው የውሸት ፕሮፖጋንዳ የተታለሉ ሰኔ 15 የሰማዕታት ቀን እናከብራለን ብሎ ሲንቀሳቀስ በነበረ ሀይል ላይ የተጠና እርምጃ መወሰዱንም ተናግረዋል።

ቡድኑ በእርምጃው ኪሳራ የደረሰበት ሲሆን፤ ሰላማዊ ዜጎች ተጠቁ የሚል የሀሰት ፕሮፓጋንዳ በመንዛት ህዝብን እያደናገረ መሆኑንም ተናግረዋል።

"አሸባሪ ቡድኑ ይህን ያህል ሰራዊት ማረኩ፣ ከተማ ተቆጣጠርኩ "እያለ የሚያሰራጨው መረጃ የሀሰት ፕሮፓጋንዳ መሆኑንም ኮሎኔል ጌትነት አረጋግጠዋል።

የኢትዮጵያ ህዝብ ቡድኑ በሚያሰራጨው የሀሰት መረጃ ሳይደናገር መንግስት ክልሉን መልሶ ለማቋቋም እያከናወነ ያለውን ተግባር እንዲደግፍም ጥሪ አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም