በኢትዮጵያ እና በራሺያ መካከል የቆየው ታሪካዊ ግንኙነት በሁሉም መስኮች ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ተገለፀ - ኢዜአ አማርኛ
በኢትዮጵያ እና በራሺያ መካከል የቆየው ታሪካዊ ግንኙነት በሁሉም መስኮች ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ተገለፀ
ሰኔ 16/2013 (ኢዜአ) ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን ከሩሲያው የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ሚስትር ሰርጌ ላቭሮቭ ጋር በራሽያ ሞስኮ ከተማ መከሩ።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ በኢትዮጵያ ወቅታዊ ሁኔታን በተመለከተ ገላፃ አድርገውላቸዋል፡፡
በትግራይ ክልል ህግን የማስከበር እርምጃ ተከትሎ የመልሶ ማቋቋም፣ ያልተገደበ የሰብዓዊ ድጋፍ፣ ለመገናኛ ብዙሃን ሽፋን እንዲሰጡ ማመቻቸት እንዲሁም ከሰብዓዊ መብት ጉዳዮች ጋር የሚነሱ ውንጀላዎችን የማጣራት ተልዕኮ እና ህጋዊ እርምጃዎችን የመውሰድ ተግባራት በትኩረት እየተከናወኑ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ስድስተኛው ሀገር አቀፍ ምርጫ ክዋኔ አስመልክቶ ሰላማዊ በሆነ መልኩ መጠናቀቁን እና በብሄራዊ ምርጫ ቦርድ መርሃ ግብር መሰረት የድምፅ ቆጠራ ውጤቶች ለህዝብ ይፋ እየተደረጉ መሆናቸውን ገልፀዋል፡፡
በታላቁ ህዳሴ ግድብ ዙሪያ የሚነሱ ጥያቁዎችን ኢትዮጵያ አሁንም አፍሪካዊ ችግሮችን አፍሪካዊ መፍትሄ የመስጠት አካሄድን በመከተል በፍትሃዊነት ላይ የተመሰረተ አቋሟን አጥብቃ እንደምትቀጥል አስረድተዋል፡፡
ከሱዳን ጋር ያለው የድንበር ግጭት በሁለቱ ሀገራት መካከል ችግሮችን በጋራ መፍቻ ስርዓት የተበጀ ቢኖርም፤ ሱዳን አጋጣሚን ተጠቅማ ወደ ኢትዮጵያ ግዛት መግባቷ ከዓለም-አቀፍ ስርዓት ውጪ መሆኑን አብራርተዋል፡፡
ከሱዳን ጋር ያለውን የድንበር ግጭት በዲፕሎማሲ ጥረት መፍትሄ ለማበጀት ኢትዮጵያ የጀመችው ጥረት በቀጣይ ተጠናክሮ እንደምትቀጥል አረጋግጠዋል፡፡
እንደ አቶ ደመቀ ገለፃ የኢትዮጵያ ህዝብ እና መንግስት ራሺያ እንደቀድሞ ሁሉ በመርህ እና የሀገር ሉዓላዊነትን ባከበረ መልኩ ለኢትዮጵያ የምታደርገውን ሁለንተናዊ ድጋፍ እና የምትወስደውን አቋም ያደነቁ ሲሆን፤ ይህ ድጋፍ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ዕምነታቸውን አስቀምጠዋል፡፡
በተጨማሪ በቀጣይ ዓመት የአፍሪካ-ራሺያ ፎረም አዲስ አበባ እንዲካሄድ በኢትዮጵያ በኩል ዝግጁ መሆኗን ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ አረጋግጠዋል፡፡
ከሩሲያው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሚስተር ሰርጌ ላቭሮቭ በበኩላቸው፣ በትግራይ ክልል መንግስት በሃላፊነት የወሰደቻቸው እርምጃዎች እና በቁርጠኝነት የሚያከናውናቸው የሰብዓዊ ድጋፍ ተግባራት የመንግስትን የሞራል ፅናት እና የፖለቲካ ብቃት ማሳያ ናቸው ብለዋል፡፡
ስድስተኛው ሀገር አቀፍ ምርጫ ሩሲያ በታዛቢነት እንድትሳተፍ መደረጉ የታሪካዊ ግንኙነቱ ከፍታን ያንፀባረቀ መሆኑን በመጠቆም፣ ምርጫው በሰላማዊ ሁኔታ ስኬታማ ሆኖ መጠናቀቁ እንዳስደሰታቸው ተናግረዋል፡፡
በታላቁ ህዳሴ ግድብ በአፍሪካ ህብረት አመቻችነት የተጀመረው ድርድር ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ራሽያ እንደምታምን፤ ለዚሁም አስፈላጊውን የቴክኒክ ድጋፍ ለመስጠት ፍላጎት እንዳላት ጠቁመዋል፡፡
ከሱዳን ጋር ያለው የድንበር ግጭት ኢትዮጵያ ሉዓላዊነቷን በሰላማዊ መንገድ ለማስከበር እና ችግሮችን በዲፕሎማሲ ለመፍታት የምትከተለውን ጤናማ አካሄድ አድንቀዋል፡፡
በኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ የሚደረገውን ማንኛውም ጣልቃ ገብነት ራሽያ እንደማትደግፍ ገልፀው፤ በሁለቱ ሀገሮች መካከል ያሉ የትብብር መስኮች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ ሚኒስትሩ አረጋግጠዋል፡፡
በተጨማሪ በቀጣይ ዓመት የአፍሪካ-ራሺያ ፎረም በአፍሪካ ህብረት መዲና አዲስ አበባ እንዲካሄድ በኢትዮጵያ በኩል ዝግጁ መሆኗ መገለፁን አድንቀዋል፡፡
በሁለትዮሽ ግንኙነቱ በተለይ በትምህርት፣ በአቅም ግንባታ፣ በሳይንስ እና ቴክኖሊጂ አጠናክረው ለማስቀጠል፤ የተፈረሙ ስምምነቶች ወደ ተግባር ለማስገባት እንዲሁም በሂደት ላይ ያሉ ስምምነቶችም በፍጥነት እንዲፈረሙ ከስምምነት ላይ ተደርሷል፡፡
በመጨረሻም ሁለቱም ሚኒስትሮች ያካሄዱት ውይይት ፍሬያማ ሲሆን በኢትዮጵያ እና በሩሲያ መካከል የቆየው ታሪካዊ ግንኙነት ትርጉም-ባለው ደረጃ በተለያዩ ዘርፎች ለማስቀጠል ቁርጠኛ መሆናቸውን ሚኒስትሮቹ አረጋግጠዋል፡፡